Fayyaan Mataa, Fayyaa Waa Maraa ti!

በእሬቻ መታሰቢያ የሻማ ማብራት ላይ የተደረገ ንግግር

በኩምሳ ቡራዩ (ምእራብ አውስትራሊያ፣ ፐርዝ)

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 2፣ 2016 በአገራችን ታርክ ላይ አስከፊ ጥላሸት የተቀባበት ቀን ነው። ምንአልባትም ይህ ጥላሸት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመደረጉ እስከአሁን ሕዝባችንን ካስከፈላቸው የታሪክ ግድፈቶች በአስከፊነቱ በላቀ ደረጃ የሚያዝ ነው። በዚህ ቀን በሚሊዮን የሚቆጥሩ የኦሮሞና የሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የእሬቻ በዓል ለማክበር ቢሾፍቱ ወደሚገኘው ሆራ – አርሰዲ አመሩ። የሰላም ምልክት፣ የፍቅር ምልክት፣ የምስጋና ምልክት፣ የአብሮነት ምልክት፣ የተስፋ ምልክት የሆኑትን የፀደይ አበባና ለምለም ሳር ይዘው ለአምላካቸው ምስጋና ለመስጠት፣ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ደግሞ ሰላምና እርጋታን ለመለመን ወደዚያ በጣም ሚስጥራዊ ወደሆነ ቦታ አመሩ። ባህላዊ ልብስ ለብሰውና ተኳኩለው በአዲስ አመት ብሩህ ተስፋ ተሞልተው፣ ወንድ፣ ሴት፣ ትልቅ፣ ትንሽ፣ ደሃ፣ ሃብታም ሳይል፣ “Birraan Bariite” – Yeroon kan keenya taate” እያለ በፍቅርና በደስታ ከዚያ ሚስጢራዊ ቦታ ደረሰ።

15140787_1475851015-1887ነገር ግን፣ በዚህ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ ከውጭ ያልመጣ፣ ግን ጠባብነቱን ለ25 ዓመታት ሲያረጋግጥ የኖረ፣ የአገሪቷን መንበረ ስልጣን በሃይል የተቆጣጠረው ቡድን ሲያስብበት ከርሞና በፍጹም ከእሬቻ ሥርዓት ውጭ የሆነውን የሞት መስተንግዶ አዘጋጅቶ ጠበቀው። ይህ ቡድን እሬቻ ከፖለቲካ ጫና ነፃ መሆኑን ጠንቅቆ እያወቀ፣ በፍጹም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የአባገዳዎችን ባህላዊ ሚናን በፖለቲካ ካድሬዎቹ ሊተካ ወሰነ። ነገር ግን ጅግናዎቹ የኦሮሚያ ቄሮዎች/ወጣቶች ባህላቸው ሲዛነፍ፣ ስርዓት ሲጣመም፣ ሕዝብ ሲዋረድ፣ እሬቻ ለፖለቲካ ጥቅም ሲውል፣ አባገዳዎች ከሚገባቸው የክብር ቦታ ሲገፉ ማየት ስለተሳናቸው በቆራጥነት ወደ መድረኩ ብቅ አሉ። ከዚያ በኋላ የሆነውን መግለጽ ልብን ያሻካራል። ጠላት ቀድሞ ተዘጋጅቶበታልና፣ ከሰማይ የጋዝ ቦንብ፣ ከምድር ደግሞ የጥይት ውርጅብኝ ለቀቀበት። ሕዝቡን በምድሩ፣ ያውም እጅግ በሚያከብረው በዓሉ ላይ በጅምላ ጨፈጨፈው። በጠላትነት ታክቲክ አደናበረውና ቀድሞ ወደአላሰበው ጉድጓድና ሐይቅ ከተተው። በአገራችን ታሪክ ትውልድ ይቅር የማይልውን የግፎች ሁሉ ግፍ ፈፀመ።

ዛሬ በእሬቻ በዓል ላይ ስንት ወንድሞቻችን/እህቶቻችን እንደተገደሉ እንኳን በግልጽ ማወቅ አልተቻለም። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሰው እሬሳ ከጉድጓድ እየወጣ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብዬው እራሱ ከ500 ሰዎች በላይ መሞታቸውን በቅርብ አመልክቶ ነበር። ሌሎች ምንጮች ግን ከ700 –1000 እንደሚደርሱ ይገምታሉ።

ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ይህ ዝም ብሎ የሚጠቀስ ቁጥር አይደለም። የሰው ልጅ ሕይወት ነው። እናትና ልጅ በአንድ ላይ ሞተዋል። ሁለት ወንድማማቾች በአንድ ላይ ተገድለዋል። አባቶችና እናቶች ሳይመለሱ እንደወጡ ቀርተዋል። ገና ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁና ተጋብተው ወራት ያልሞላቸው፣ ልጅ ወልደው ለመሳም በጉጉት የሚጠባበቁ ሙሽራዎች አልፈዋል። አገራችን በሃዘን ላይ ናት። ሕዝባችን በሃዘን ላይ ነው። ያ እልቂት አልበቃ ብሎት ከዚያ በኋላም በኦሮሚያ ዞኖች በሙሉ ወያኔ የጅምላ ጭፍጨፋውን ቀጥሏል። አሁን እኛ እዚህ ተሰብስበን የቢሾፍቱን እልቂት በምናስታውስበት ጊዜ ብዙዎች እየተገደሉ ናቸው። ይህ በፍጹም ሃላፊነት የማይሰማው ጠላት በሃይል ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሞት ሽረት እያደረገ ነው።  እንዲያውም ይባስ ብሎ የመግደል፣ የማሰር፣ የመሰወር፣ የመዝረፍ ፈቃድ ለራሱ ሰጥቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብሎ ሰላማዊ ሰዎችን በተቃዋሚነት እየፈረጀ ማዋከቡን ተያይዞታል።

ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ይሁን እና አንድ ተስፋ አለ። ሕዝባችን በ25 ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት በዚህ አምባገነን ላይ ተነስቷል። በኦሮሞ ቄሮዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ የተመታው የፍርሃት ድባብ የነፃነት ነጸብራቅ፣ መተሳሰብን እና አብሮነትን በሚገባ አሳይቷል። አዎን፣ ወያኔ ይህንን ተስፋ ማጨለም አልቻለም። አዎን፣ ከጨለማው በስተጀርባ ብርሃን ይታያል። የሕዝባችን አንድነት የወያኔን የመግደል የፈቃድ ጊዜ እያሳጠረበት ይገኛል። ሕዝባችን መተሳሰቡን፣ መቻቻሉን፣ መዋደዱን፣ አብሮነቱን፣ በቃል ሳይሆን በተግባር፣ ከቦረና እስከ ጎንደር፣ ከሐረርጌ እሰከ ባሕርዳር፣ ከጋምቤላ እሰከ ባሌ፣ ከኮንሶ እስከ ወለጋ፣ ከወሎ እስከ ወሊሶ፣ በአጠቃላይ የአገራችን ክልልሎች እያስመከረ ይገኛል። ይህ የትግል አንድነት መንፈስ ወያኔውን አሸብሮታል። በቢሾፍቱ ለተጎዱ ወንድሞቹና እህቶቹ በየሆስፒታሉ ተራ ይዞ ደሙን ለመለገስ የተሰለፈው፣ አማራው፣ ጉራጌው፣ ሃዲያው፣ ከምባታውና ከሁሉም ብሄረሰብ ነው። ከዚህ በላይ መተሳሰብ የለም። “የአንተን ደም በኔ ደም ተካና በሕይወት ኑር” ከማለት የበለጠ አንድነት የለም። ሕዝባችን ይህንን በማድረጉ ብቻ የወያኔን የፖለቲካ መሠረት አፍርሶታል። ወያኔ ኦሮሞን ለብቻ፣ አማራን ለብቻ፣ ጋምቤላን ለብቻ፣ ሱሪናውን ለብቻ፣ ኮንሶውን ለብቻ በማድረግ መግደልና መቆጣጠር እንደ ፖለቲካ ስልት ተያይዞት ነበር። ሕዝባችን ኦሮሞውን፣ አማራውን፣ ጋምቤላውን፣ ሱሪናውን አትንካብን እያለ ነው። ወገኖቼ፣ አንድነታችን የወሰን ብቻ አይደለም፡፤ የብሔራዊ ጥቅምና የብሔራዊ ተስፋ አመላካች እንጂ።

ወያኔው ከትግራይ ሕዝብ አብራክ መወለዱ የሚካድ አይደለም። ነገር ግን ይህ ሃላፊነት የማይሰማው ወንበዴ የትግራይ ሕዝብ ሙሉ ውክልና አለው ማለት እጅግ የተሳሳተ ነው። እንዲህ ያለ አቀማመር የትግራይ ሕዝብ የእሬቻን ጭፍጨፋ፣ የጎንደርን እልቂት፣ የባሕር ዳርን ግፍ ይደግፋል እንደማለት ይቆጠራል። በእኔ አመለካከት፣ ይህ የተሳሳተ አደማመር ነው። ምክንያቱም፣ በእኩልነት የሚያምኑ፣ ኢሰብአዊነትን የሚያወግዙ፣ እንደነ አብርሃ ደስታ ያሉ ኢትዮጵያኖች በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥም አሉ። በዚያም አንፃር የኢትዮጵያ ሕዝብ በሃዘን ልቡ ተሰብሮ እያለ፣ በግፍ የፈሰሰው የዜጎቻችን ደም ሳይደርቅ አሸሸ ገዳሜ የሚያስነኩ የትግራይ ልጆችም አሉ። እነዚህ እንደ አጋዚ ጦር ዘመን የማይሽረው፣ ትውልድ የማይረሳውን፣ ታሪክ ይቅር የማይለውን ወንጀል መፈጸማቸውን መርሳት የለባቸውም። እኛ እያዘንን እነሱ ይደንሳሉ። ምን የሚባል ዳንስ ነው? የትኛውስ አንጀት አስቻላቸው? እንዴትስ አስተዋይና አዋቂ ከመሃላቸው ጠፋ?

ወገኖቼ፣ ጊዜ ገድቦ መናገር ይከብዳል እንጂ የጊዜ ጉዳይ ነው። ጊዜውን ጠብቆ ከነመሰሪ ሥራው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ይወርዳል። ይሁንና፣ የመወገጃውን ጊዜ ማፋጠንም ሆነ ማዘግየት የእያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ነው። በየጊዜው የምንጮህ ብቻ ከሆነ ሕዝባችንን እየገደለና እየተንገዳገደ የአራት ኪሎ ቆይታው ይራዘማል። ተግባራችንን ከወሬ በላይ አድርገን በሚቻለን ሁሉ በአንድነት፣ በጽናትና በብስለት የምንገፋ ከሆነ፣ እንኳንስ ይኽንን አናሳ ቡድን ቀርቶ ማንኛውን አካል ከሕዝብ ፍርድ የማምለጥ አቅም የለውም። ይህንን አምባገነን ማስወገድ ማለት የእናቶችን ለቅሶና የአባቶችን ውርደት ማስቀረት ነው። ትውልድን ከሞት፣ ሃገርን ከውርደት መታደግ ነው።

ወያኔ እኛን የማባላት፣ እኛን የማራራቅ የፖለቲካ ሴራ ይተዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በተለይም የኦሮሞውን እና የአማራውን ሕብረተሰብ ማናከስ የፖለቲካው ዋና ሥራ ነው። የሁለቱ ብሄረሰብ መግባባት ወደ 70% የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያካትት ስለሆነ ለዚህ ከ6% በታች የማይሆነውን ማህበረሰብ እወክላለሁ ለሚለው ሴረኛ ቡድን እስከ አጥንቱ ዘልቆ ያስፈራዋል። ለዚህ ነው አንዱን ጠባብ፣ ሌላውን ትምክህተኛ ብሎ እየፈረጀ እስከዛሬ የዘለቀው። ያ እቁብ አሁን ተበልቶበታል። ያ ሴራ አሁን ተነቅቶበታል። እኛን በታሪክ ላይ እያጣላን የእሱ የፖለቲካ ሥልጣን ላይ መንደላቀቅ ማብቃት አለበት። ታሪክን ለታሪክ ትተን ፖለቲካን ከወያኔ እጅ መንጭቀን ማውጣት አለብን። እያንዳንዳችን ከትናንት ይልቅ በነገው ላይ ትኩረት መስጠት አለብን። ትላንት ታሪክ ሆኗል፣ ነገ ግን ተስፋ ነው። ተስፋችን ደግሞ ከወያኔ አምባገነን ሥርዓት ነፃ የወጣችና በሕዝባችን መፈቃቀድ፣ በዲሞክራሲና በእድገት የጎለበተች ኢትዮጵያን መገንባት ነው።

ወገኖቼ፣ መፈራራትና አለመተማመንን እየቀነስን፣ መወያየትን፣ መተዋወቅን እና መግባባትን እያዳበርን መሄድ አለብን። በአገራችን ብዙ አብዮቶች ተካሂደዋል። የተገኙ መብቶችም አሉ። ነገር ግን ዘላቂ ዲሞክራሲያዊ ሥስርዓትን እስካሁን መገንባት አልቻልንም። ሁሉንም ብሄረሰቦች እኩል የሚያገለግል ሥስርዓት ማዋቀር አልቻንም። በዚህ ላይ በሚገባ አስበን የአገራችንን እና የሕዝባችንን ሁኔታ የተሻለ ለማድረግ በያለንበት መጣር አለብን። አንዱ የሌላውን ጥቅም ማሰብ መጀመር አለበት። ጭፍን ብሄርተኝነት የፖለቲካን እና የኢኮኖሚ እኩልነትን ይገድባል፤ ሰላምና መረጋጋትን ሊያመጣ ከቶም አይችልም፤ ፍትሐዊ አብሮነትን ይጎዳል። ነገር ግን፣ የእሱ ደም የእኔ ደም ነው ካልን፣ የእሱ ሰላም የእኔ ሰላም ነው ካልን፣ የእሱ ጥቅም የእኔም ጥቅም ነው ካልን፣ እውነተኛ ፌደራሊዝም የበለጠ ያቀራርበናል እንጂ አያጣላንም። ስለዚህ በያለንበት የሕዝባችንን መብት እንዲከበር፣ ሠላምና መረጋጋት በአገራችን እንዲሰፍን፣ ዜጎች ሃለፊነታቸውን እና ግዴታቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማድረግ በጽኑ መንቀሳቀስ አለብን። በምንደግፋቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ተገቢውን ጫና እያደረግን፣ በአማባገነን ላይ የሚደረገውን ትግል በአንድነት እንዲያፋጠን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀው አብይ ጉዳይ ነው።

ሃዘናችንን ለመካፈል ለመጣችሁ ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን።
ሃገራችንን እግዚአብሔር ይጠብቅልን!
ስለአዳመጣችሁኝ አመሰግናሉ።
ኩምሳ ቡራዩ

(ኦሮሞ ኮምዩኒቲ- ምእራብ አውስትራሊያ፣ ፐርዝ)