Fayyaan Mataa, Fayyaa Waa Maraa ti!

የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች የባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት በተስፋፊ የሶማሌ ክልል መሪዎች ሴራ አይበጠስም

ጅባ ሮሮ (ከሆሮ)

አፋን ኦሮሞ እንደተናጋሪው ሕዝብ ብዛት በቃላት ብቻ ሳይሆን በተረት፣ በፈሊጣዊ አነጋገሮች፣በምፀታዊ አባባሎች በአጠቃላይም በሥነ ቃል እጅግ የበለፀገ ነው፡፡ የሶማሌ ክልል መሪዎችን የእብደት ተግባር ሳስብ ከእነዚህ የሥነ ቃል ሀብቶቻችን አንዱ ታወሰኝ፡፡
ኦሮሞ ነገረኛና በጥፋት ሥራው ሁሉንም የሚበክል ሰውን በአጭሩ ሲገልፀው “ጭራዋን በደም የተነከረች ጊደር; (Raada eegee dhiigaa) ብሎ ይጠራዋል፡፡ ጭራዋ በደም የተነከረች ጊደር ጭራዋን ስታወዛውዝና ስታወራጭ በአጠገቧ ያሉትን ሁሉ በደም ትበክላለች፣ ለራሷ ቆሽሻ ሌሎችንም ታቆሽሻለች፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እንደ ጊደር በቆሻሻ ተግባሩ ሌላውን የሚያቆሽሽ፣ሰው እርስ በርስ እንዲጠራጠር የሚያደርግና በራሱ ወንጀል ሌሎችንም ያለሃጢያታቸው ለችግር የሚዳርግ ሰው አለ፡፡ ለዚህ ነው ጭራዋ ደም ከተነከረ ጊደር ይሰውረን (Raada eegee dhiigaa nurraa haa qabu) የሚባለው፡፡
12ከላይ እንደገለጽኩት ይህንን አባባል ያስታወሰኝ የአሁኑ የሶማሌ ክልል አመራር የግዛት ማስፋፋት ህልሙን ዕውን ለማድረግ በሚል ፈሊጥ በኦሮሚያ ክልል የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ላይ እያካሄደ ያለውን የወረራ ተልዕኮ ለማሳካት በተያያዘው መቅበዝቀዝ በሰላማዊ የኦሮሞና የሶማሌ ክልሎች ተጐራባች ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የጥላቻ ዘር ለመዝራት እያደረገ ያለው ሙከራ ነው፡፡ ጀብደኛውና አምባገነኑ አመሪር የሶማሌ ክልል ሕዝብ ፍላጐት ያልሆነውን ከኦሮሚያ ወረዳዎች መሬት የመንጠቅ የወረራ ዘመቻ የሶማሌ ክልልና የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ግጭት በማስመሰል ለዘመናት በሰላም አብሮ በመኖር የሚታወቀውንና በማንም ሴራና ደባ ሊበጠስ የማይችል ቤተሰባዊ ቁርኝት የፈጠሩትን የሁለቱን ክልል ሕዝቦች በአርቴፊሻል የጥላቻ ድንበር ለመለያየት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
አምባገነነኑ የሶማሊ ክልል አመራር መቼም የማይሣካውን እኩይ ዓላማውን ማራመድ የሚችለው ሁለቱ ሕዝቦች በጥርጣሬና በጥላቻ አየተያዩ ሲጋጩና ሲገዳደሉ መሆኑን በመገንዘብ የሶማሌ ክልል ሕዝብን በፀረ-ኦሮሞ ኘሮፖጋንዳ ለሚታለልና የእኩይ ተግባሩ ፈጻሚ መሣሪያ ለማድረግ ከንቱ ሲለፋ ይታያል፡፡ መላ ሐረርጌና የደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች የሶማሌ ክልል እንደሆኑ እየሰበከ የሶማሌ ክልል ሕዝብ በዚህ የማታለያ ወጥመድ ውስጥ ገብቶ በኦሮሞ ወንድሙ ላይ ብረት እንዲያነሳ ለማነሳሳት በከፍተኛ ደረጃ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ እንደዚሁም በሰላማዊ የኦሮሚያ ክልል የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ላይ የታጠቀ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በማዝመት ህዝብን እያስገደለና እያስዘረፈ የኦሮሞ ሕዝብ ድርጊቱን የሶማሌ ክልል ሕዝብ የፈፀመው መስሎት በሶማሌ ክልል ወንድሞቹ ላይ ቂም እንዲቋጥርና የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ ከንቱ ሙከራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር የሰላምና የሕዝቦች አንድነት ፀር የሆነው የሶማሌ ክልል ጀብደኛ አመራር በኦሮሞ አርብቶ አደር ላይ እየፈፀመ ያለው ጥቃት የፌዴራል መንግስት እጅ ያለበት በማስመሰል የኦሮሞ ሕዝብ በራሱ ልጆቹ ከፍተኛ ተሳትፎ በተደራጀውና የኦሮሞና የመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንካራ ክንድ በሆነው የፀጥታ ኃይልና የፌዴራል አመራር ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም የተወሰኑ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሥልጣናትን በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመግዛት ከጐኑ አሳልፎ የመላ የአገሪቱ ፀጥታ ኃይል ድጋፍ አብሮት እንዳለ በማስመሰልና በዚህም ራሱን በማታለል የጀብደኝነት ተግባሩን ሲገፋበት ይታያል፡፡ በዚህ ድርጊቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትን በኃይልና በአሉባልታ ለመናድና ቀን ከሌት ለሚራወጡ ፀረ ሰላምና ፀረ-ሕዝብ አሸባሪ ወገኖች ፀረ ኢትዮጵያ ኘሮፖጋንዳ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በወንድማማች ሕዝቦች መካከል እንዲሁም በእህትና አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ጭምር አለመተማመን ለመፍጠርና በዚህም ቀዳዳ ሾልኮ የመሬት ማስፋፋት ጀንዳን ለማሳካት ሌት ተቀን በመፍጨርጨር ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ሴራው በመንግስትና በፀጥታ ኃይሉ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በሕዝቡ ተሳትፎ እየተጋለጠ በመምጣቱ መያዣ መጨበጫ ያጣው ይህ ጨፍጫፊ ቡድን ጭራዋን በደም ነክራ እያወዛወዘች ሁሉንም እንደምትበክል ጊደር አሁንም ዘዴውን እየቀያየረ በጥፋት መንገዱ ላይ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡
pafd1-e1460331244435ለነገሩ የዛሬው የሶማሌ ክልል አመራር ተስፋፊና አምባ ገነን ነው ስንል በኦሮሞ ላይ እየተካሄደ ያለው ጥቃት በሁሉም አመራር የተደገፈ ነውማለታችን አይደለም፡፡ ከአመራሩ መካከል የተወሰኑት በኦሮሞ ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት የሚያወግዙና የመስፋፋት አላማን የሚቃወሙ ነገር ግን አቋማቸውን በግልጽ ለማሣየት የቸገራቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት አምባ ገነኑ የሶማሌ ክልል መሪ ኦሮሚያን የመውረር አጀንዳ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአባላት ባቀረበበት ወቅት በከፍተኛ አብላጫ ድምጽ የተሸነፈ ሲሆን አምባገነኑ መሪም በዚህ በመናደድ የተቃወሙትን አመራሮች ያለአንዳች ይሉኝታ ከኃላፊነታቸው በማባረር እንደፈለገው የሚያሽከረክረውን አዲስ አመራር በራሱ አምሳል ማዋቀሩ ይታወሳል፡፡ ሆናም ግን ከእነዚህም አመራር አንዳንዶቹ ወረራን የማይደግፉና እርምጃ ይወሰድብናል ብለው በመስጋት ሁኔታውን በዝምታ በመከታተል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ አይፈረድባቸውም፡፡
ምክንያቱም የዛሬው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አምባ ገነን መሪ አብዲ መሐመድ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከአዲስአበባ ጭምር ሰው አፍኖ እየወሰደ የሚያስር አዲሱ ዝያድ ባሬ ነው፡፡ የራሱን ሚስጥራዊ እስር ቤት አዘጋጅቶ ዜጋን በማሰርና በማሰቃየት የሚታወቅ ለህገ መንግስትና ለህግ የማይገዛ ጨካኝና ጀብደኛ ግለሰብ ነው፡፡ ይህ ጀብደኛ ግለሰብ በኦሮሞ ላይ ብቻ ሣይሆን በራሱ የሶማሌ ክልል ሕዝብ ላይ ጭምር በከፍተኛ ጭካኔ እርምጃ በመውሰድ በክልሉ ውስጥ ፍራቻን ያሰፈነ የዲሞክራሲና የፍትህ ጠላት ነው፡፡ የአብዲ እስር ቤት ተብሎ በሚታወቅ ስውር እስር ቤት ለዓመታት በመሠቃየት ላይ የሚገኙ ንፁሃን ዜጐች ለዚህ አባባላችን ተጨባጭ ማስረጃ ናቸው፡፡
ስለሆነም የክልሉን መሪ ፖርቲ ኘሬዚዳንት ጭምር እንደ አሻንጉሊት በመቁጠር ያለ እኔ ማን አለ? በሚል ትዕቢት በክልሉ ውስጥ አምባገነንነትን ያሰፈነ ጀብደኛን ከህዝብ ነጥሎ መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡
ይህ የበቀለ ፀረ-ዴሞክራሲ አረም በቶሎ ካልተነቀለ በኦሮሞና በሶማሌ ተጐራባችና ወንድማማች ሕዝቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በአገር ላይም የሚያደርሰው የፖለቲካ ኪሣራና ጥፋት ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡
ይህንን የተስፋፊ ፀረ ሰላም ኃይሎች የጥፋት ሴራ በእንጭጩ ለመቅጨት ከወዲሁ መንቃት ይገባል፡፡ በተለይም የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች የድንበር አካባቢ ነዋሪ ኦሮሞዎችና ሶማሌዎች ይህን ሴራ ተገንዝበው ፈጥነው ለማክሸፍ ከወዲሁ ዝግጁ መሆኖ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከድንበር አካባቢ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ እየደረሰበት ያለው ጥቃት በሶማሌ ክልል አምባገነን አመራር የጥፋት እጅ እንጂ በወንድሙ የሶማሌ ሕዝብ አለመሆኑን በመለየት ረገድ ያለው ግንዛቤ ጥሩ በመሆኑ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ከሩቅ ያሉና በአሉባልታ ወሬ ጭምር የተሳሳተ አቅጣጫ ይዘው እየተጓዙ ያሉ አንዳንድ ወገኖችም በየዋህነትም ሆነ በቅንነት ወገኖቹ በሶማሌ ሕዝብ እየተጠቁ እየመሰላቸው በአጠቃላይ ሶማሌ ላይ ጥላቻ እንዳያሳድሩ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ችግሩና ጥፋቱ የጥቂት በቢሮ ውስጥ የሸፈቱ አምባገነን የሶማሌ ክልል አመራሮች የተፈጠረና እየተመራ ያለ መሆኑን በመገንዘብ እነዚህን ወገኖች ከሕዝቡ ነጥሎ ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡
17796155_10155178348144483_6864976727823910290_nበዚህ ረገድ የኦሮሚያ ክልል አመራር በድንበር አካባቢ ያለውን ኦሮሞ እያሰቃዩ ያሉት የሶማሌ ክልል ጀብደኛ አመራሮች እንጂ ሕዝቡ አለመሆኑን እንዲረዳ በማድረግ በኩል ጥሩ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እያሳዩ ያሉት ተነሳሽነት የሚያስመሰግን ነውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡
በተለይም በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሶማሌ ክልል ተወላጆችና አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ ተስፋፊው ቡድን የተያያዘውን የጥፋት ድርጊት በግልጽ በመቃወም እየወሰዱ ያሉት አቋም የሚደነቅና ሊበረታት የሚገባው ነው፡፡ በዚህ በኩል አንዳንድ የሶማሌ የጐሳ መሪዎች ጭምር አምባገነኑ አመራር ከጥፋት እንዲቆጠብ በማሳሰብና ልጆቻቸው የጥፋት ተግባሩ ተሳታፊ እንዳይሆኑ በማድረግ እያከናወኑ ያሉት ቅን ተግባር በስፋት እየታየ መሆኑ እጅግ የሚያስደስት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የሶማሌ ተወላጆች ኡጋዞች (የጐሣ መሪዎች) ጭምር በጥፋት ኃይሉ መታሠር መጀመራቸው በስፋት እየታየ ነው፡፡ ይህም የሁለቱ ሕዝቦች ለዘመናት የቆየ ወንድማማችነት በተወሰኑና በአላፊ ጠፊ ፀረ ሰላምና አምባ ገነን ግለሰቦች ሴራና ተንኮል ሊደፈርስ እንደማይችል በተጨባጭ ያሳየ በመሆኑ ለሕዝቡ ያለን አክብሮትና ምስጋና እጅግ የላቀ ነው፡፡
በአጠቃላይ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች በዚህ ወሳኝ ወቅት ለጋራ ጠላታቸው ጀብደኛ አድራጐት ሳይበገሩ በመካከላቸው የተሸረበውን ሴራ ለማክሸፍ አንድነታቸውን አጠናክረው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝብ ሁሌም ነዋሪ ነው፡፡ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዝምድናም ቀጣይ ነው፡፡ ፀረ ሰላምና ፀረ አንድነት የሆነው ድንበር ገፊው የሶማሌ ክልል ጀብደኛ አመራር ደግሞ የጧት ጤዛ ነው፡፡ የሀቅ ብርሀን ሲወጣ ይጠፋል፡፡ ጭራዋን በደም ነክራ ኮምታቆሽሸን ጊደር የምንገላገልበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም፡፡
የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች ወንድማማችነት ለዘላለም ይኑር፡፡

ምንጭ: የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች  ግንኙነት