Fayyaan Mataa, Fayyaa Waa Maraa ti!

የፊንፊኔ መልከዓምድራዊና ታሪካዊ ዳራ

የኦሮሚያ ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት የኦሮሞ ክልል(ኦሮሚያ) አንድ አካል እና እምብርት የሆነችው ፊንፊኔ መጠሪያ ስሟን ያገኘችው በከተማዋ ማዕከላዊ ሥፍራ ከምድሯ ማህፀን የሚያፈልቀውን የተፈጥሮ ፍል ውሀ ምንጭን መሰረት በማድረግ
ነው፡፡ በወቅቱ ፊንፊኔ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢና ዙሪያው ከኦሮሞ ጎሳዎች አንዱ የሆነው የቱለማ ጎሣ ከሶስቱ ዐቢይ ጎሳዎች(“Balbala”) አንዱ የሆነው የዳጪ ንዑሳን ጎሳዎች የሆኑት የጉለሌ፣ የኤካ፣ የገላን እና የአቢቹ ጉሳዎች ይኖሩበት እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡ እነዚህ ጎሳዎች በ12 መንደሮች በመከፋፈልና በየራሳቸው የጎሳ መሪዎች ይተዳደሩ እንደነበር በወቅቱ የነበሩትን የጎሳ መሪዎች ስም በመዘርዘር ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህ የአካባቢ ጎሳ መሪዎች መካከል እነ ቱፋ ሙና፣ ዱላ ሃራ፣ ጂማ ጃተኒ፣ ጉቶ ወሰርቢ፣ ጂማ ጢቂሴ፣ አቤቤ ቱፋ፣ ዋሪ ጎሎሌ፣ ቱፋ አረዶ እና ሞጆ ቦንሳራ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተለይም ፊንፊኔ የጉለሌ ኦሮሞ ጎሳዎች የሚበዙበት እንደነበረች በ1868 አካባቢ በካቶሊክ
ሚሲዮኖች የተፃፉ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል አፄ ሚኒሊክ ቤተ መንግስታቸውን በእንጦጦ ላይ ከማድረጋቸው በፊት በመስከረም 1868 ዓ.ም በፊንፊኔ አካባቢ ካቶሊክ ሚሲዮኖች “የፊንፊኔ ሚሲዮን” በሚል መጠሪያ ቤተክርስቲያንና የዕምነት ማስፋፊያ ጣቢያዎች ከፍተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና በዚህም ፊንፊኔ በመልማትዋ ምንሊክ መቀመጫውን ወደ አከባቢው እንዲያዛውር በዋነኝነት እንደገፋፋቸው በወቅቱ የነበረ ሉዊፊ ላሴሬ የተባለው ሚሲዮን ፅፏል፡፡ ሌላው ምክንያት አፄ ሚኒሊክ አያታቸው “…አንቺ ምድር ዛሬ “…ች” ሞልተውብሻል፤ ነገር ግን ወደፊት የልጄ ልጅ ቤት ሰርቶብሽ ከተማ ትሆኛለሽ” በማለት ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ እንደነገራቸውና እቴጌም ባላቤታቸው ደቡብን ለመውረር በመጡበት ጊዜ ከባላቤታቸው ጋር ለጤናቸው ጉዳይ ወደፍል ውሃ ሄደው በነበረበት ወቅት ከነበሩበት ድንኳን ውጭ በመንዝ አካባቢ አይተው የማያውቁትን አበባ አይተው በመደነቅ አዲስ አበባ በማለታቸው ከ1887 ጀምሮ ፊንፊኔ – አዲስ አበባ መባል ጀመረች፡፡ የኦሮሞን ባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የአከባቢዎችም ነባር ስያሜዎች ለውጥ/መቀየር አንድ ተብሎ ተጀመረ፡፡
በሚኒሊክ የጦር አበጋዞች በመላ ኦሮሞ አካባቢና የደቡብ አካባቢዎች ላይ አጠቃላይ ወረራ እስከታወጀበት እ.ኤ.አ 1870 በነበረው ጊዜ እርሻና ከብት እርባታን የኑሯቸው ዋነኛ መሰረት በማድረግ በፊንፊኔና አካባቢዋ ይኖሩ የነበሩት የኦሮሞ ተወላጆች እንደተቀረው የኦሮሞ ሕዝብ ሁሉ በገዳ ሥርዓት ይተዳደሩ የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ ፊንፊኔ በኦሮሞ ክልል እምብርት ሥፍራ ላይ የምትገኝ መሆኗም የንግድና የአምልኮ ማዕከልም መሆን አስችሏታል፡፡ በገዳ ስርዓት ኦዳ ነቤ ሥነ-ሥርዓት በድምቀት ከሚከናወንባቸው የኦሮሞ መሬት ክፍሎች አንዷም ነበረች፡፡ ምንም እንኳን የፊንፊኔ ኦሮሞዎች በባህላቸው መሰረት ከራሳቸው፣ ከተፈጥሮና ከአካባቢያቸው ጋር ተስማምተው በዚህ ማዕከላዊ በሆነ ስፍራ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሰላም መኖራቸው የሚያጠያይቅ ባይሆንም በፊንፊኔና በዙሪያዋ በነበሩ የኦሮሞ ማህበረሰቦች ላይ ከሰሜኑ አጎራባች ደጋማ ክፍል በሚነሱ ማህበረሰብ ተወላጆች ወረራና ዝርፊያ ይካሄድ የነበረው ሚኒሊክ የሸዋ ንጉስ ከመሆናቸውም አስቀድሞ እንደነበር በወቅቱ በስፍራው የነበረው የእንግሊዙ የዲፕሎማቲክ ልዑክ ሻለቃ W.C Harris [የኢትዮጵያ ደጋማ ክፍሎች The Highlands of Ethiopia, (1884)] በሚል ባሳተመው የጉዞ ማስታወሻ መፅሀፉ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
በሂደት ወደ አጠቃላይ ወረራ የተቀየረውና በሚኒሊክ ወራሪ ጦር ድል አድራጊነት የተጠናቀቀው ዘመቻ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢውን የኦሮሞ ተወላጆች ለሞት፣ ለአካል መጉደልና ስደት ዳረገ፡፡ ከሞትና ስደት የተረፉት የመላ ኦሮሚያና የደቡብ ሕዝቦችም ነፃነታቸው ተገፎ በባርነት ቀንበር ስር ወደቁ፡፡ መሬታቸውን ተቀሙ፡፡ ሃብት ንብረታቸው በወራሪው ተዘረፈ፡፡ ግፍና በደሉ በዚህም አልበቃ ብሎ ፊንፊኔ ከወራሪው ጦር መቀመጫነት ወራሪውን ጦር ተከትለው የመጡ ነዋሪዎች መስፈሪያ ከተማ ሆነች፡፡ የፊንፊኔ ነባር ነዋሪዎች ከርስታቸው ተነቅለው ለወራሪው ሹሞች ተሰጡ፡፡ ለዚህ አስከፊ ተግባር ህጋዊ መሰረትና ድጋፍ ለመስጠት ሲባል በ1907 እ.ኤ.አ የመሬት አዋጅ(Land Charter) ተከትሎ በወጣው ማስታወቂያ የፊንፊኔ ነባር ኦሮሞዎች ካርታ ያልወሰደ በመሬቱ ከመቀመጥ በስተቀር መሬቱ ያንተ አይደለም ተባለ፡፡ የፊንፊኔ ነባር የኦሮሞ ተወላጆች በገዛ መሬታቸው ጪሰኛ ሆኑ፤ በእምነትና ባህላቸው መሰረት አምልኮአቸውን እንዳይፈፅሙ ታግደው የወራሪውን እምነት የመቀበል የመከራ ቀንበር በግዳጅ በላያቸው ላይ ተጫነ፣ ከዚህም አልፎ የጉለሌና የኤካ ጉሳዎች ሊመናመኑ ችለዋል፡፡
በወራሪው ጨቋኝ ገዢ የፊንፊኔ ነባር የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የወደቀው ግፍና መከራ በግድያ፣ በምርኮ፣ ከርስት መነቀልና በጭሰኝነት ጉልት ሥርዓት በማደር ብቻ ያበቃ አልነበረም፡፡ በኦሮሞ ተወላጅ ላይ እንደተጫነው የወራሪው ባህል ሁሉ በኦሮሞ ባህልና የቋንቋ ስያሜ ይታወቁ የነበሩ የፊንፊኔና ዙሪያዋ አካባቢዎች የከተሞችና የቦታ ጥንታዊ መጠሪያዎች እንዲቀየር ተደረገ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ፊንፊኔ የሚለው የጥንት መጠሪያዋ በሃይል ተቀይሮ “አዲስ አበባ” በሚል ስያሜ ተተካ፡፡

የጥንት/ቀድሞ መጠሪያ-                   በሳባ መጠሪያ-                             አዲስ መጠሪያ
Agamsa-                                   አገምሳ-                                      መርካቶ
Doobbii-                                   ዶቢ-                                         ቀጨኔ
Hurufa Boombii-                 ሁሩፈ ቦምቢ-                                 ጃንሜዳ
Dildila-                                     ድልድለ –                                     እንጦጦ
Eekkaa –                                  ኤካ-                                             የካ
Birbirsa Gooroo –                 ቢርቢርሰ ጎሮ-                                 ፒያሳ
Caffee Araaraa-                   ጨፌ አራራ-                                   አራት ኪሎ
Malkaa Daabus-                  መልካ ዳቡስ-                                  ቸርቺል ጉዳና
Caffee Tumaa-                    ጨፌ ቱማ-                                    ስድስት ኪሎ
Caffee Aannanii-               ጨፌ ኣነኒ-                                    ሜክሲኮ
Qarsaa-                                     ቀርሳ-                                      ካዛንቺስ
Baddaa Ejersaa-                     በዳ ኤጀርሳ-                              ራስ ካሳ ሰፈር
Mujjaa-                                   ሙጃ-                                        ሽሮ ሜዳ
Garbii-                                  ገርቢ-                                            ሰንጋ ተራ
Golboo-                               ጎልቦ-                                            ቄራ ቂርቆስ
Calcalii-                              ጨልጨሊ-                                       ሳር ቤት
Roobii-                                ሮቢ-                                              ነፋስ ስልክ
Burqaa Finfinnee-              ቡርቃ ፊንፊኔ-                                 ፍልውሀ
Tulluu Heexoo-                  ቱሉ ሔጦ-                                 ትልቁ ቤተመንግስት
Lupha Kormaa                    ሉጳ ኮርማ                                  ራስ ብሩ ሰፈር
Baaroo Kormaa               ባሮ ኮርማ                                     ራስ ተሰማ ሰፈር
Hrbuu Irrechaa               ሐርቡ እሬቻ                                  ራስ ሀይሉ ሰፈር
Karra Qirixi                      ከራ ቂሪጢ                                   ሰሜን በር
Adami                               አዳሚ                                      ሰሜን ማዘጋጃ
Babo                                   ባቦ                                            አዲሱ ቄራ
Burqa Qoricha                  ቡርቃ ቆርቻ                                የካ ሚካኤል
የነፍጠኛው ድርጊት የኦሮሞ ጥንታዊ ስሞችን መቀየር ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ጥንታዊ ስያሜዎችን በማዛባትም ጭምር ግፍ የተሰራ መሆኑ ለምሳሌ፡- ሀቃቂ ወደ አቃቂ፣ ቀሊቲ ወደ ቃሊት፣ ቀበነ ወደ ቀበና፣ ኤካ ወደ የካ…ወዘተ አዛብቶ እንዲጠሩም የተደረጉ እስከ ዛሬም ምስክሮች ናቸው፡፡
በሚኒሊክ እግር የአገዛዙን ሥርዓተ-መንበር የተቀበሉት አፄ ኃ/ሥላሴም ነባሩን የኦሮሞ ተወላጅ ከመሬቱ የማፈናቀል እና ማንነቱን የመፋቅና የመደምሰሱን እርምጃ ከአፄ ሚኒሊክ ባልተናነሰ ይልቁንም በረቀቀና በመጠቀ የትምህርትና ባህል ፖሊሲ በመቅረፅ አጠናክረው ገፉበት፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ከሀገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ውስጥ በማግለልና በመግፋት ባህል እና ቋንቋው እንዲጠፋ የተጠናከረ ዘመቻ አካሄዱበት፡፡ ነባሩ የኦሮሞ ተወላጅ ራሱ በመሰረታት ከተማ ከገዛ መሬት ከመፈናቀል አልፎ በቋንቋው እንዳይማር እንዳይገለገል በተቃራኒው ባይተዋር ተደርጎ በባህል በቋንቋው እንዲሸማቀቅ ተደረገ፡፡
ኦሮሞ ራሱ በመሰረታት ፊንፊኔ በ1960 ዓ.ም ማብቂያ አካባቢ የመሬት ይዞታ መረጃ እንደሚያመላክተው የመሬት ይዞታ ክፍፍሉ ከመሬቱ 50 በመቶ ያህሉ በመኳንንትና መሳፍንቱ እጅ የነበረ ሲሆን፣ 33 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የእምነት ተቋማት ሥር ወድቆ እንደነበር ተጨባጭ የጽሁፍ መረጃዎች ያረጋገጡት እውነታ ሲሆን ነባሩ የኦሮሞ ተወላጅ ግን ከይዞታው እየተነቀለ ወደ አልለማውና በወባ ነዲድ በተወረረው ወደከተማዋ ጥግ በመግፋት በከተማው መሃል የኦሮሞ ተወላጅ ቁጥር አናሳ እንዲሆን ተደረገ፡፡
እግር በግር የተተኩት የአፄ ሥርዓቶች በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የጫኑትን የመከራ ቀንበር የኦሮሞ ሕዝብ ያለተቃውሞ አሜን ብሎ የተቀበላቸው አልነበሩም፡፡ የመጫና ቱለማ የመረዳጃ ማህበር የዚሁ የሰላማዊ አመፅ መገለጫ ነው፡፡ የባሌ ኦሮሞ ገበሬዎች አመፅም እንዲሁ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ የመብት ጥያቄዎች እና አመፆች የኦሮሞን ሕዝብ ወደድል ባይመሩትም ለ1966ቱ ዓ.ም ሕዝባዊ ንቅናቄ እርሾ ለመሆናቸው በወቅቱ ይስተጋቡ የነበሩት የመሬት ላራሹ፣ የብሔርና የዲሞክራሲ መብት ጥያቄዎች ማስረጃ ተደርገው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ የአፄውን መንግስት በሀይል ገልብጦ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት የገዛው ወታደራዊ መንግስት ለእነዚህ ሕዝባዊ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ባህሪም ሆነ መሰረት ያልነበረው የአፄዎቹ ተቀጥላ ከመሆን ያለፈ አልነበረም፡፡ በመሆኑም የብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ጥያቄን ፈታሁ በሚል በሀይል የተጫነን አንድነት በህዝቦች ላይ አጠናክሮ በመጫን የኦሮሚያን ሀብትና የኦሮሞ ወጣቶችን የስልጣን ዘመኑ ተጀምሮ እስከጨረሰ ላኬሄዳቸው ጦርነቶች መስዋዕት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም መላ ሀገሪቷ በጦርነት እሳት ከጫፍ እስከጫፍ ከመንደዷ በተጨማሪ ሕዝቦቿም የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ሆነው በአስከፊ የድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲማቅቁ ያደረጋቸው መሆኑ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፤ ደርግ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ አትሞ ያለፈው ጥቁር የታሪክ ጠባሳ በአንድ በኩል የጭቁን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲ እና ለብሄር መብት መረጋገጥ የሚየደርጉት ትግል በየማዕዘኑ ተፋፍሞ እንዲቀጣጠል ያደረገ ሲሆን ይህም እስካልተረጋገጠ ድረስ ሀገሪቷ ከጦርነት ወደ ጦርነት ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ እንጂ የሰላምም ሆነ የልማትን ጭላንጭል የማየት እድል እንደማይኖራት ሁሉም የዲሞክራሲ ሀይሎች በገሀድ የተረዱበት ዘመን ነበር፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በአጠቃላይ የፊንፊኔ ነባር ተወላጆች የቱለማ ጎሳዎች እና ሌሎች ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች በፊንፊኔ ላይ ያላቸውን “የልዩ ጥቅም” ሥረ-ነገር ከዚህ የታሪክና የህግ መብት የሚመነጭ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ የሚሆነውም በዚህ የተነሳ ነው፡፡

ለተጨማሪ መረጃ:  የኦሮሚያ-ክልል-በአዲስ-አበባ-ላይ-ያለው-ልዩ-መብት-አዋጅ