Fayyaan Mataa, Fayyaa Waa Maraa ti!

የአቃቤ ህግ የቪዲዬ ማስረጃዎች በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ቀረቡ፡፡

(ኦሮሚዲያ, የካቲት 17, 2017) የነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ለየካቲት 10 ተቀጥሮ የነበረው አቃቤ ህግን የሲዲ ማስረጃ ለመመልከት ነበር። በዛሬው ችሎት አቃቤ ህግ ስለ ሲዲዎቹ ይዘት ተጠይቆ፤ 4ት ሲዲዎች እንዳሉ እና 2ቱ ሲዲዎች በ4ኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ ላይ፣ 1ዱ ሲዲ 5ኛ ተከሳሽ አብደታ ነጋሳ ላይ እንዲሁም የተቀረው አንድ ሲዲ 11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዶ ላይ የቀረቡ እንደሆነ ተናግሯል።

16826032_1294884180548248_8673960022647508645_oበበቀለ ገርባ ላይ የቀረቡት ሁለት ሲዲዎች ሶስት ቪዲዮዎችን የያዙ ሲሆን፤ ሶስቱ ቪዲዮዎች አቶ በቀለ ገርባ ለኢሳት ቴሌቪዥን የሰጡት ቃለመጠይቅ፣ ለኦኤምኤን ቴሌቪዥን የሰጠው ቃለመጠይቅ እና ኦሮሞ ጥናት ማህበር (OSA) ላይ ያደረገው ንግግር ሲሆን አቃቤ ህግ “ለኦነግ ልሳን ለሆኑት ለኢሳት እና ለኦኤምኤን የተሰጡ መግለጫዎች በተጨማሪም ኦሮሞ ጥናት ማህበር( OSA) ላይ ያደረገው ንግግር አመፅን እና ሁከትን ቀስቃሽ እንደነበሩ ያሳዩልናል” ሲል የቪዶዎቹን ጭብጥ ገልፅዋል። የ5ኛ እና 11ኛ ተከሳሾችን በተመለከተ ከላፕቶፓቸው የተገኘ ቀስቃሽ ቪዲዮዎች መሆናቸውን ተናግሯል። OSA ( የኦሮሞ ጥናት ማህበር) ምን ማለት እንደሆነ ዳኞች አቃቤ ህጉን ጠይቀውት ምን ማለት እንደሆነ እንደማያውቅ ተናግሯል።

በመጀመሪያ በችሎት ቀርቦ የታየው የቪዲዮ ማስረጃ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ የቀረበው ለኢሳት ቴሌቭዢን በታህሳስ ወር 2008 ላይ “ሰብአዊ መብቶች” የተባለ ፕሮግራም ላይ በኦሮሚያ ስለተነሳው ተቃውሞ አቶ በቀለ በስልክ የሰጡትን አስተያየት የያዘ የ 44 ደቂቃ ቪዲዮ ነው። በቪዲዮው ላይ አቶ በቀለ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩንቨርስቲዎች ስለተነሱ ተቃውሞዎች እንዲሁም አዳማ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ጠይቀው መከልከላቸውን ሲገልፁ ተደምጧል። በመጨረሻ ላይም የመከላከያ ሰራዊት በሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚወስደው እርምጃ የተገቢ እንዳልሆነ ገልፀው፤ ሰራዊቱ ህዝቡን መከላከል እንዳለበት እና በወንድሙ ላይ ቃታ መሳብ እንዲያቆም ምክር የሰጡትን አስተያየት አቃቤ ህግ በማስረጃነት አቅርቧል፡፡

በመቀጠል የታየው ቪድዮ አቶ በቀለ ገርባ የኦሮሞ ጥናት ማህበር (OSA 2015) ላይ ያደረጉት የ36 ደቂቃ ንግግር ነው። የኢህአዴግ መንግስት በኦሮሞዎች ላይ ያደረገውን እና እያደረገ ያለውን የመብት ጥሰት በዝርዝር ያስረዱበት ንግግር ሲሆን፤ ነፃነታቸውን ማግኘት እና ከጭቆና ለመላቀቅ ሰላማዊ የትግል ስልትን መከተል እና ነውጥ አልባ (nonviolent) እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ መጠቀም እንደማይገባ በተደጋጋሚ ሲናገሩ በቪዲዮው ላይ ታይቷል።

በ2012 በሚኖረው ሃገራዊ ምርጫም ፓርቲያቸው ኦፌኮ በየቀበሌው ወርዶ በሰፊው የመንቀሳቀስ እቅድ እንዳለው፤ ይህም ከፍተኛ ስራ እንደሚጠይቅ ቢሆንም መሳካቱ እንደማይቀር ሲናገሩ ታይተዋል–አቶ በቀለ በቀረበው ቪዲዮ ላይ። በመጨረሻም አቶ በቀለ ንግግሩን አድርገው ሲጨርሱ አርቲስት ያደሳ ቦጂያ በራሱ የተሰራ የበቀለን ምስል በስጦታነት ሲያበረክትላቸው ታይቷል።

ሁለቱ ቪዲዮዎች ከታዩ በኋላ የምሳ ሰአት በመድረሱ ቪደዮ መታየቱ የተቋረጠ ሲሆን፤ ከሰአት እንደሚቀጥል ዳኞች ሲገልፁ አቃቤ ህግ ከሰአት እንደማይችል በማሳወቁ ቀሪዎቹን ሲዲዎች በመጪው ሰኞ (የካቲት 13/2009) ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ከውጪ የመጣ የአቶ በቀለ ዘመድ ማረሚያ ቤት ሄዶ እንዳይጠይቃቸው ስለተከለከለ በችሎት መገናኘት እንዲፈቀድላቸው በማለት የአቶ በቀለ ጠበቃ አቶ አብዱልጀባር ለዳኞች ጥያቄ አቅርበው ነበር። ማረሚያ ቤት ሄዶ እንዳይገባ የተከለከለውን የአቶ በቀለ ዘመድ ዳኞች ለምን መግባት እንዳልቻለ ጠይቀውት ምክንያቱ ሳይጠቀስለት መግባት እንደማይችል እንደተከለከለ ለዳኞች ምላሽ ሰጥቷል።

የማረሚያ ቤት የጥበቃ ሃላፊ ኢትዮጵያዊ የሆነ ቤተሰብ እስረኛ መጠየቅ እንደማይከለከል ገልፀዋል። የአቶ በቀለ ዘመድ የካናዳ ፓስፓርት ያላቸው ያመሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ዳኞች ጉዳዩን ለማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እንዲያመለክት እና ምላሽ ካላገኘ ሰኞ በሚኖረው ቀጠሮ በችሎት ለመገናኘት እንደሚፈቅዱላቸው ገልፀውለታል።

Source: https://www.facebook.com/ehrproj/

[fbl_login_button redirect=”” hide_if_logged=””]

Leave a Reply

Your e-mail address will not be published. Required fields are marked *