Fayyaan Mataa, Fayyaa Waa Maraa ti!

እሬቻ—የምስጋና፣ የእርቅ፣ የአንድነት፣ የሠላም እና የደስታ ቀን! 

—ቂም ተይዞ ወደ እሬቻ አይኬድም! –
#ዮሴፍ_ሙለጌታ_ባባ, PH.D.

እሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እንደ ቅዱስ በዓል ይከበራል። እሬቻ የምስጋና፣ የእርቅ፣ የአንድነት፣ የሠላም እና የደስታ ቀን ነው። እሬቻ በዓል ለዋቃ ጉራቻ—ምሉዕ በኩለሄ አምላክ—ምስጋና የሚሰጥበት ቀን ነው። የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ዋቃዮ—Waaqaayyoo—ነው። ዋቃዮ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነው። ኃይሉ ወሰን የሌለው ነው፤ ሁሉን ነገር የሚያውቅ እና ሁሉ ቦታ የሚገኝ ነው። ዋቃዮ ትክክለኛ ዳኛ እና የፍትሕ አባት ነው።

ስለዚህ፣ ሕዝቡ ለዚ መልካም ስጦታ ከልብ የመነጨ ምስጋና ለአምላኩ የሚያቀርብበትና “የዋቃዮ ስጦታ ተመልሶ ለዋቃዮ የምሰጥበት ቅዱስ በአል ነው” ብሎ ከልቡ ያምንበታል። እሬቻ ማለት “ስጦታ” ማለት ነው። እሬቻ ማለት ለተከበረ ነገር የሚከፈል ዋጋ ማለት ነው። በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለምለም ሣር የሰላምና የብልጽግና ምልክት በመሆኑ፣ በእሬቻ በዓል ላይ የሚሳተፈዉ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ይህንን ለምለም ሣር በሁለት እጆቹ በመያዝ አምላኩን ያመሰግናል። በኦሮሞ ባህል እርጥብ ሣር ህይወትን የሚያሳይና ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው ነው:: ከሁሉም በላይ ክረምቱን ከበረዶ፣ ከከባድ ነፋስ፣ ከጎርፍና ከውርጭ የታደጋቸውን ታላቅና ቅዱስ አምላካቸውን አንድ ላይ ሆኖ ያመሰግናሉ። መኸሩንና አስመራውን ደግሞ እንድባርክላቸው ወደ ፈጣሪ ይጸልያሉ። ስለዚህ የእሬቻ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሻገረ አምላክ የሚሰጥ የክብር ዋጋ ነው።

ሀገር በቀል የሆኑ የእምነት በዓላትን የመገንዘብና የማብራራት ችግር ያለባቸው ኢትዮሮፕያንስ (Westernized Ethiopians)፣ የእሬቻ በዓልን በተሳሳተ መንገድ ስረዱ ይታያሉ። ለምሳሌ፤- በበዓሉ ላይ የሚደረገዉን የአምልኮ ሥነ- ሥርዓት በመመልከት፣ ሕዝቡ ዋቃዮን ሳይሆን ውሃውን አልያም ሰይጣንን ‹‹እንደሚያመልክ›› አድርጐ ይረዳሉ። ኦድላይ ሶቴቪንስን “በአቶሚክ ቦንብ ዉስጥ ሰይጣን የለም፣ በሰዎች ልቦና እንጂ” እንዳለ ሁሉ፣ ሰይጣን በእነዚህ ሰዎች አእምሮ እና ልብ ውስጥ እንጂ በውሃ ውስጥ አይኖርም። ሰይጣን ዳክዬ ወይም ጉማሬ አይደለም—ካልጠፋ ቦታ ውሃ ወስጥ ምን ይሰራል! ባይሆን የሰይጣን ትክክለኛ አድራሻና ማደርያ የሰው ልቦና ነው። ስለዚህ፣ኢትዮሮፕያንስ ሰይጣንን ‹ልባቸው› ውስጥ ይፈልጉት! በእርግጥ ኢትዮሮፕያንስ (Westernized Ethiopians) ትምህርት-ቤት ተመላለሱ እንጂ አልተማሩም!

በተቃራኒው ውሃ የሕይወት ምልክት ነው። ለዚህም ነው በእሬቻ በዓል ጊዜ ውሃና ልምላሜ እንደ ዋቃዮ ስጦታ የሚታዩት። ያለ ውሃ ሕይወት ቀጣይነት የለውም። ውሃ ዋቃዮ ለፈጠራቸው ልጆቹ የሰጠ ፀጋ ነው። ድሪቢ ደምሴ ቦኩ እንዳለው፤

‹‹ኦሮሞ፣ ወንዝ፣ ጫካና ተራራ ይወዳል፤የተፈጠረበትና ፍቅር ያገኘበት ስለሆነ በየዓመቱ ለምለም ሣርና የፀደይ አበባ ይዞ ለእሬቻ ወንዝ ውሃ ዳርቻ በመሄድ፤ ተራራ ላይ በመውጣት፤ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል። በጤና፣ በሰላም፣ ለሰውና ለከብት እርባታ እንዲሰጠውም ይጸልያል።››

ስለዚህ፣ አንድ ሃማኖት የተከበረና የበላይ ሌላው የተናቀና የበታች አድርጎ ማቅረብ በማንኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም።በሃይማኖት ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት ከተፈለገ፣ ሃይማኖታዊ ልዩነቶቻችን ላይ ሳይሆን፣ የጋራ ሃይማኖታዊ እሰቶቻችን (ፍቅር፤ ሰላም፤ደስታ፣ ፍትሕ፣ ቅንነት፣ መልካም አሳቢነት፣ መከባበር…ወዘተ) ላይ ማተኮር የግድ ይላል። ‹‹ፍቅር መግዛት ከፈለግህ፣ ፍቅር ራሱ መክፈል ያለብህ ዋጋ ነው›› እንደሚባለው የእኛ እምነት ወይም አመለካከት እንዳይነካብን ከፈለግን፣ የሌላውን ሃይማኖት ፈጽሞ ማጥላላትና መናቅ የለብንም። ‹‹የለሎች ሃማኖት ጨርሰው መደምሰስ›› የሚል የድንጋይ ዘመን ፍልስፍና፣ በዘመኑ ዓለም ውስጥ (in contemporary world) ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። የሌላውን ሃይማኖት እየናቁ የራስን ማክበር በሳልነት አይደለም። ማንኛውም ሰው ነፃ-ፍቃዱን ተጠቅሞ የፈለገውን ሃይማኖት፤ እምነት እና አስተሳሰብ የመከተል ወይም የመያዝ ተፈጥሯዊ መብት አለው።

ቅዱሳት መጽሐፍትም ይህንን እውነታ ያረጋግጣሉ፤ ‹‹የፈለገ ይመን የፈለገ ይካድ›› (አል-ከህፍ 29) ‹‹በፊታችው ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ›› (ኦሪት ዘዳ. 30፡ 19)

በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 27 ማንም ሰው ያመነበትንና ህልናው የፈቀደውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመከተል ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው በግልጽ ያስቀምጣል።

‹‹እግዝአብሔር አንዱን ሐይማኖት ብቻ የሚወድ ቢሆን የሚወደውን የዓለም ሃይማኖት አድርጎ የቀሩትንአያጠፈቸውም? እሱ ካላጠፋቸውስ ማን ሊያጠፋቸው ይችላል? ከሱ የበለጠ እሱ የሚወደውን ነገር እናውቃለን?እንግድህ እግዝአብሔር በዕውቀቱ የሚያኖራቸውን ልዩ ልዩ ሃይማኖት የያዙ ሰዎች በልዩነት ማየትን እንተው።›› (አቤ ጉበኛ፤ አልወለድም፣ ገጽ. 81-82)

‹‹The question that one has to ask is, what right has anybody got of telling you that the God of your people who has preserved you all these years (otherwise you would not be there), is a false God? To say that the God of a particular people is untrue is to declare that those people are themselves not quite people. This statement is fully illustrated by the examples in history where some nations were brutally exterminated without raising much trouble in the conscience of their exterminators because the former were ‘worshippers of false Gods.’” (Kihumbu Thairu, 1975, pp. 67-68)

እንግዲህ እሬቻ—የምስጋና፣ የእርቅ፣ የአንድነት፣ የሠላም እና የደስታ ቀን መሆኑን ስለምያስታዉሰን ይህንን በዓል ስናከብር:-

(1ኛ) በምዕራቡ ዓለም የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ተጽእኖ ምክንያት ናላቸዉ የዞረባቸው ኢትዮሮፕያንስ (Westernized Ethiopians) ሕዝቡን ‹‹ፓስታ እንዴት እንደሚበላ›› እና ‹‹ወይን እንዴት እንደሚቀዳ›› ማስተማሩን ወደ ጎን አድረገው ልቦና እንድገዙ፣ አድርባይነታቸውን እንዲተው እና ከብዙኃኑ ሕዝብ ጋር እንድታረቁ ወደ ዋቃ ጉራቻ እንፀልያለን፤

(2ኛ) ዋቃዮ ለሀገራችን አንድነት፣ ፍቅር እና ዘላቅ-ሠላም እንድያመጣልን እንጸልያለን። በተለይ ለሆዳቸው ሳይሆን ለህሊናቸው ብቻ ስሉ ሕዝባቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችን ዋቃዮ ሀብታቸውንና ልጆቻቸውን እንድባርክላቸው ወደ ዋቃዮ ጉራቻ እንጸልያለን፤ እኛም እንወዳቹዋልን—እናከብራቹዋለን!

በተቃራንው በሕዝብ ስም የሚነግዱ ሆዳሞች፣ ወንጀለኞች፣ ሙሰኞች፣ ነፍስ ገዳዮች፣ ሌቦች፣ አጨበርባሪዎች፣ አስመሳዎች፣ አሳዳጊ የበደላቸው የመንግስት እና የሃይማኖት ሌቦች ወዘተ… ዋቃዮ የሕዝቡን ለቅሶ ሰምቶ በታላቅ ክንዱ ወደ ፍርድ እንዲያመጣልን ለምለም ሣር በሁለት እጆቻችን በመያዝ ዋቃዮን እንማጸናለን። ሆዳም ሰው እምብርት የለውምና ለእናንተ ክብር የሚባል ነገር የለንም !

(3ኛ) ‹‹ከመጠምጠም መልካም-ሥራ ይቅደም›› የሚለውን ‹ፍልስፍና› ችላ በማለት ስለ ድሆች አሰቃቅ ሁኔታ ሳይሆን፣ ስለ ‹‹ፔንሲዮን›› እና ‹‹ዶላሪዝም›› አብዝቶ የሚያስቡ የመንግስት ባለስልጣናት እና የኅይማኖት አባቶች እንደ አሸን ፈልቷልና፣ ዋቃዮ የ‹‹ሳፉና ሳፌፋና›› ምስጥር እንድገልጥላቸው ለምለም ሣር በሁለት እጆቻችን ይዘን ወደ እርሱ እንፀልያልን፤

(4ኛ) ስለ አህምሮው ሳይሆን፣ ስለ አለባበሱና ሆዱ ብቻ አብዝቶ የሚጨነቅ ወጣት ትውልድ ተፈጥሯልና፣ ዋቃዮ ጉራቻ
‹ልብስ› ሳይሆን ‹ልብ›
‹ጋቢና› ሳይሆን ‹ልቦና›
‹ፎቅ› ሳይሆን ‹ሐቅ›
‹ድራፍት› ሳይሆን ‹ድፍረት›
እንድሰጣቸው ለምለም ሣር በሁለት እጆቻችን ይዘን ወደ እርሱ እንፀልያልን!

(5ኛ) ቂም ተይዞ ወደ እሬቻ አይኬድምና በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት መካከል እውተኛ እርቅ/ሠላም እንድወርድ እንፀልያለን! ከሁሉም በላይ፤ ለዚች ሀገር የሚያስፈልጋት ሠላም ነው! ዘላቅ ሠላም! ሮናልድ ሬገን ያለውን ግን እንዳንረሳ ‹‹ሰላም የግጭት አለመኖር አይደለም፤ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅም ነው፡፡›› ስለዚህ፣ ከራሷ ጋራ ሠላም የፈጠረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአንድነት እንስራ። ማርቲን ሉተር ኪንግ እንደሚለን ‹‹ጦርነትን ማወጅ የለብንም ማለት ብቻ በቂ አይደለም፤ ሠላምን መውደድና መስዋዕትነት መክፈልም ይኖርብናል፡፡›

በመጨረሻም የእሬቻ ቅዱስ በዓል ጸሎትን አንድ ላይ እንጸልያልን፡-
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!
ሀዬ! የእውነትና የሰላም አምላክ!
ሀዬ! ጥቁሩና ሆደ ሰፊው ቻይ አምላክ!
በሰላም ያሳደርከን በሰላም አውለን!
ከስህተትና ከክፉ ነገሮች ጠብቀን!
ለምድራችን ሰላም ስጥ!
ለወንዞቻችን ሰላም ስጥ!
ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!
ለሰውም ለእንስሳቱም ሰላም ስጥ!
ከገዳ ባህላችን ከዋቄፋና እምነታችን ጋር አኑርልን!
አንድነታችንን አጠንክርልን!
ትናንሾቻችንን አኑርልን!
ጤነኛና ብልህ ልጆች ስጠን!
ወላድ በጤና ትገላገል!
የወለደችውን አሳድግላት!
ሕጻን በእናቱ እቅፍ ይደግ!
ለወላድ ጤናና ዕድሜ ስጣት!
ላልተማረው እውቀት ስጥልን!
ኦ አምላክ አደራጀን!
አደራጅተህ አታፍርሰን!
ተክለህ አትንቀልን!
የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ
ፈጥረህ አትዘንጋን!
ክፉውን ያዝልን!
ከወንጀልና ከወንጀለኛ አርቀን!
ምቀኛና ቀናተኛውን ያዝልን!
ከመጥፎ አየር ጠብቀን!
ንጽሕ ዝናብ አዘንብልን!
ያልንተ ዝናብ የእናት ጡት ወተት አይሰጥምና!
ያላንተ ዝናብ የላም ጡት ወተት አይሰጥምና!
ያለንተ ዝናብ መልካው ውሃ አይሰጥምና!
ያላንተ ዝናብ ምድሩ ቡቃያ አይሰጥምና!
ከእርግማን ሁሉ አርቀን!
በአባቱ ከተረገመ አርቀን!
በእናቷ ከተረገመች አርቀን!
እውነትን ትቶ ከሚዋሽ አርቀን!
ከረሀብ ሰውረን!
ከበሽታ ሰውረን!
ከጦርነት ሰውረን!
ልጄ እያሉ አልቅሶ ከመቅበር ሰውረን!
በጥቁር ፀጉር ከመሞት ሰውረን!
በነጭ ፀጉር ከመደህየት ሰውረን!
አርሶ ምርት ከማጣት ሰውረን!
ከሌላ ሰው ጦስ ሰውረን!
ከከፉ ነገር ሁሉ ሰውረን!
ገዳው የሰላም፣ የልምላሜና የድል ነው!
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!
(ምንጭ፡- ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ፣ የኢትዮሮፒያንስ የአስተሳሰብ ቅሬ፣ ገጽ. 71-73)

Leave a Reply

Your e-mail address will not be published. Required fields are marked *