Fayyaan Mataa, Fayyaa Waa Maraa ti!

ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ጃዋርንና OMN(ን) ከሰሱ፣ዲፕሎማቱና የዓለም አቀፍ ህግ ባለ ሙያው ባይሳ ዋቅ-ዋያ የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል።

ስለ ጃዋር እና ጃዋር በዳይሬክተርነት ስለሚመራው OMN ስለሚባለው የሳቴላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። በስዎ አባባል የድርጅቱ ዳይሬክቴርም ሆነ ድርጅቱ ራሱ “የጥላቻ ንግግርንና ጽንፈኝነትን” እንዲያስፋፉ መንግሥት ድጋፍ የሰጣቸው እንደሆነና፣ በግለሰቡም ሆነ በድርጅቱ ላይ አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ ባገሪቷ ላይ የሩዋንዳ ዓይነት የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide) ሊከሰት ይችላል የሚለው ነው። የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሰረቱ፣ የሆነ የሰው ልጅ ዘርን ከሌሎች ለይቶ ለማጥፋት በተግባር የሚውል የተቀነባበረ የወንጀል ሥራ ስለሆነ፣ በዛሬው ሁኔታ ይህንን አሰቃቂ ወንጀል ለመፈጸም እየተዘጋጀ ያለው የኢትዮጵያ ብሄርና የወንጀሉም ዒላማ የሚሆነው ብሄር የትኛው እንደሆነ ሳይነግሩን እንደው በደፈናው “እመኑኝ” እውነቴን ነው የምላችሁ “የዘር ማጥፋት ወንጀል” በ OMN እየተተለመ ነው ይሉናል። እንደ አንድ ዜጋ ሥጋትዎን መግለጽዎ አግባብ ሆኖ እያለ፣ እንደው ዝም ብሎ ያላንዳች አስተማማኝ ማስረጃ ግለሰብንም ሆነ ድርጅትን መወንጀል ግን ካንድ የሕግ ባላሙያ ነኝ ከሚል ግለሰብ የሚጠበቅ አይደለም። ምናልባት እስዎ የለመዱት ያኔ በደርግ ዘመን በጥርጣሬ ብቻና ያላንዳች ሕጋዊ ማስረጃ ያንድን ትውልድ ምርጥ ዘር በቀይ ሽብር፣ የፊውዳል ርዝራዥ ወይም ቀይ መንገደኛ እያላችሁ ዜጎችን በጅምላ መግደላችሁ ትዝ ብሎዎት ከሆነ፣ እባክዎን ከዕንቅልፍዎ ይባንኑ። ያ በታሪካችን ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ አልፏል። ዛሬ ያለው መንግሥት “መርምረን እናስራለን እንጂ አስረን አንመረምርም” የሚል ስለሆነ፣ ግለሰቡም እንዲታሰርና ድርጅቱም እንዲዘጋ ከፈለጉ ያለዎትን መረጃና ማስረጃ በይፋ ቢያቀርቡ፣ ሁላችንም ከጎንዎ ተሰልፈን መንግሥት በሁለቱም ላይ ባስቸኳይ እርምጃ ወስዶ አገራችንን፣ እስዎ በዓይኔ አያቻለሁ ስለሚሉትና ብዙዎቻችን ግን በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን ብቻ ካየነው የሩዋንዳ ዓይነት የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲታደገን በሰልፍ እንወጣ ነበር።
በዓለም አቀፍ ሕግ፣ “የዘር ማጥፋት ወንጀል” በግለ ሰብ ሳይሆን በአንድ በተደራጀ ቡድን ወይም የፖሊቲካ ሥልጣን ባለው ኃይል የሚተገበር፣ የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ነው። በኔ ግምት የርስ በርስ ጦርነትና “የዘር ማጥፋት ወንጀል” የተማታብዎት ይመስለኛል። አዎ! አገራችን ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል ብዙ ምልክቶች ይታያሉ። እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ሰማንያ ስድስት ብሄርና ቋንቋ እንዲሁም የተለያዩ ኃይማኖቶችን የምታስተናግድ ደሃ አገር ይቅርና፣ እንደ ሱማሌ ሊቢያና የመንን የመሳሰሉ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ፣ ከሞላ ጎደል አንድ ኃይማኖት የሚከተሉ ሕዝቦችም ከርስ በርስ ጦርነት ስላልዳኑ፣ ሥጋታችን አግባብነት አለው። እርስዎን ያስፈራዎት ግን የርስ በርሱ ጦርነት ሳይሆን፣ OMN በተባለው “ጽንፈኛ” ጣቢያ አማካይነት በሚሠራጨው “የዘር ማጥፋት ወንጀል” ቅስቀሳ መሠረት የሆነ “ግምታዊ” ብሄር በሆነ “ግምታዊ” ብሄር ላይ ተነሳስቶ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይፈጽማል የሚለው ግምታዊ “ሥጋት” ነው። በኔ ግምት ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ማለትም የሌለን እንቅስቃሴ እንዳለ አቅርቦ፣ አንድ ብሄር በሌላው ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊፈጽም እየተዘጋጀ ነው ብሎ መቀስቀስ ራሱ ወንጀል ነው ብሎ ሌላ ተቆርቋሪ ዜጋ ሊከስዎት ይችላልና ቢያስቡበት መልካም ይመስለኛል። በተረፈ ግን፣ OMN የግለሰብ ንብረት ሳይሆን በተለያዩ መስኮች ዝናን ባተረፉ የምሁራን ቦርድ የሚመራ የኦሮሞ ሕዝብ አንጡራ ሃብትና የመላው የኦሮሞ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እያገለገለ ያለ ጣቢያ ስለሆነ ይህንን ሕዝባዊ ጣቢያ ይዘጋ፣ ወይም ፈቃዱን ይነጠቅ ብለው ሲለፍፉ፣ ጥላቻዎ ከዳይሬክተሩ ከጃዋር ጋር ሳይሆን ከመላው የኦሮሞ ሕዝብ ጋር እንደሆነ ቢረዱት ይበጃል ባይ ነኝ።
ጃዋርን በተመለከተ፣ ራሱን ለመከላከል እንኳን “አንድ ሻለቃ” ጦር ይቅርና አንድ ባታሊዮንን ሊመክት የሚያስችለው ሰብዓዊ ክህሎት አለው ብዬ ስለምገምት፣ “እሱን ለሱ” ልተወው። እኔን ያሳሰበኝ የስዎ፣ OMNን በቱትሲዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም ሲሰብክ ከነበረውና በጽንፈኛ ሁቱዎች ይተዳደር በነበረው የሩዋንዳው RTLM ጋር ማመዛዘንዎ ነው። ይህ አባባልዎ፣ አንድም የ OMNን ታሪካዊ አመጣጥ በውል ካለማወቅ አለያም ደግሞ፣ “አንድ ግምታዊ ብሄርን ከዘር ማጥፋት ወንጀል ለማዳን” በሚል ሰበብ ድርጅቱ እንዲዘጋ መትጋትዎ፣ ሆን ብለው በጣቢያው ተጠቃሚ አርባ ሚሊዮን ኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያለዎትን ጥላቻ በእጅ አዙር ለመግለጽ የፈለጉ መሰለኝ። ይህ እጅግ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። የፈለጉትን ለመውደድ ያልፈለጉትን ደግሞለየመጥላት መብትዎ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ብዙ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ውስጥ OMNን ብቻ ያላንዳች አሳማኝ ማስረጃ ነጥለው ለመምታት ማነጣጠጥርዎ ግን አነሰ ቢባል ቅንነት የጎደለው አካሄድ ይመስለኛል። ግን ለምን ያን ሁሉ መንገድ መጓዝ አስፈለገዎት?
የኦሮሞ ሕዝብ ዘመናዊዋ ኢትዮጵያ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በብሄራዊ የሬዲዮ ጣቢያ በቋንቋው የተላለፈው ፕሮግራም ደርግ ሥልጣን በወሰደ ሰሞን ነበር። አዎ! ያ የሰላሳ ደቂቃ የኦሮሚኛ ፕሮግራም ያኔ በትምህርት ቤት እንዳንማረውና በየመንግሥት መሥርያ ቤትም እንዳንገለግለበት የተከለከልነውን ቋንቋችንን በብሄራዊ ሬዲዮ ስንሰማው ለብዙዎቻችን ዘጠነኛው ደመና የገባን ያህል ነበር ይመስጠን የነበረው። ዛሬ ላይ ሆኔ ሳየው ግን፣ ያኔ በዚያች ሰላሳ ደቂቃ ውስጥ ያገር ውስጥና የውጭ አገር ዜና ተሰምቶ፣ የፍየል ወጠጤ ተዘፍኖበት፣ የተገደሉት ወይም የተያዙት ባላባቶች ስም ዝርዝር ተነግሮበት፣ ለአንድ ወይም ሁለት የኦሮሚኛ ዘፈን የሚበቃ ጊዜ መኖሩ በጣም ያስገርመኛል። ታዲያ ከዚያ የአንድን ብሄር ቋንቋ ከፍ አድርጎ የሌሎቹን ከሚያሳንስ ወይም ሌላ ቋንቋ እንዲነገር ከማይፈቅድ ሥርዓት ተነስተን ዛሬ በኦሮሚኛ ቋንቋ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀኑን ሙሉ ወደሚያስተላልፍ ዘመን ስንሻገር፣ ለኛ ለኦሮሞዎች የሚሰጠን ልባዊ ደስታ ለስዎ ዓይነቱ የዚያኛው “ሥርዓት ናፋቂዎች” ግን ለምን እንደማይመቻችሁ ሁሌም አልገባ ያለኝ ነገር ነው። አልገባ ብሎዎት ነው እንጂ OMN፣ መላው የኦሮሞ ሕዝብ በዘመናት ትግሉ ውስጥ ውድ ዋጋ ከፍሎበት ያመጣውና የትግሉ ፍሬ ከመሆኑም በላይ፣ ጣቢያው የኦሮሞን ሕዝብ ባሕልና ሥነ ጽሁፍ ለማሳደግ፣ ማህበረሰባዊ ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንጂ የማንንም የኢትዮጵያን ብሄር ህገ መንግሥታዊም ሆነ ሰብዓዊ መብት የማይጥስ ስለሆነ፣ ከስዎ ጎራ ስለሚነዛው በጭፍን ጥላቻ ላይ ለተመሠረተ ክስ መስሚያ ጆሮም የለንም። አትረፍ ያለው በሬ ቆዳው ለከበሮ ይውላል እንዲሉ፣ እስዎም ዕድሜ ልክዎን የኖሩት ያንድን ብሄር የበላይነት የሚያራምደው ሥርዓት በብሄሮች እኩልነት ሥርዓት መለወጡ ያልተመቸዎት ስለሆነ ዕድሜ ልክዎን ሲለፉ ይኖሯታል እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ካሁን በኋላ ወደዚያ የጨለማ ሕይወት አይመለስም። OMNም የማንንም ብሄር መብት ሳይነካ፣ የተቋቋመበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የመላው የኦሮሞን ሕዝብ የማያወላውል ድጋፍ ተንተርሶ መትጋቱን ይቀጥልበታል።
ስለ “ዘር ማጥፋት ወንጀል” ካነሱ አይቀር ዘንዳ፣ እስዎ ያላንዳች ምክንያት OMNን ከሩዋንዳው RTLM ጋር ያመሳሰሉበት የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል ማስረጃ እንደሌለዎት በርግጠኝነት ለመናገር እችላለሁ። የOMNን ፕሮግራሞች መከታተል ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን፣ እደግመዋለሁ፣ አንድም ቀን አንድም ፕሮግራሙ ያንድን ሕዝብ መብት ሲጥስ ወይም አንድን ብሄር ለማሳነስ ሲውል አላስተዋልኩም። ምናልባት ኦሮሚኛ ቋንቋ አለመቻልዎና እንደ አብዛኛው ጓደኞችዎ ለግምትዎ ቅርጽ ያበጁት በወሬ ወሬ ላይ ተመርኩዘው ከሆነ፣ በቀረችው የዕድሜ ዘመንዎ ኦሮሚኛን ቢማሩት፣ በተሳሳተ ወይም የተጣመመ ትርጉምን እንደ ዋቢ ይዞ ይህን መሰል መሠረት ቢስ ክስ አቅርበው ራስዎን ከማስገመት ይድኑ ይሆናልና ያስቡበት ባይ ነኝ።
ውድ ሻለቃ! የህትመት፣ የድምጽና የቪዲዎ ፕሮግራሞች የሚያስተላፏቸው መልዕክቶች ልክ እንደ ኑክሌር ኃይል የመግደልም የማዳንም ባህርይ አሏቸው። ወሳኙን ሚና የሚጫወተው መልዕክት አስተላላፊው ነው፤ በዚህ መልኩ ከታየ፣ የሚያጠያይቀው ቅንነትዎ ነው እንጂ የሚዲያን አሉታዊ ሚና አንስተው ስጋትዎን መግለጥዎ አግባብነት አለው። በኔ ግምት OMN ያንን አሉታዊ ሚና አይጫወትም ባይ ነኝ እንጂ፣ ሌሎች የግል የሚዲያ ተቋማት እስዎን ያሳሰበውን ህዝቡን ወደርስ በርስ ግጭት ሊመራ የሚችል አሉታዊ ፕሮግራም በተደጋጋሚ ያቀረቡ እንዳሉ አምናለሁ። በዚህ ደረጃ ከሚፈረጁት ተቋማት ለምሳሌ አንዱ ESAT ነው። እኔ ከስዎ በተሻለ ሁኔታ ESATን በዘር ማጥፋት ወንጀል እንኳ ባይሆን በሕዝቦች መካከል ጥላቻን በማስፈን ከ RTLM ያላነሰ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በመረጃና ማስረጃ የተደገፈ ክስ ለማቅረብ እችላለሁ። ይስሙኝማ!
እንደሚገባኝ ከሆነ፣ ESAT በግለሰቦች መዋጮ የተቋቋመና የሚተዳደር የግል የሚዲያ ተቋም ነው። ለዓመታትም ልክ እንደ OMN የኢትዮጵያ ሕዝብ ጆሮና ዓይን ሆኖ፣ ወገኖቻችን ከሌላ ምንጭ ሊያገኙ የማይችሏቸውን አሳሳቢ ጉዳዮችን ለሕዝብ ሲያደርስ የኖረ ድርጅት ነው። በዚህ ሥራውም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ተዓማኒነት አግኝቷል። አንዳንዴ ግን ልክ እንደ ማንኛውም የሚዲያ ተቋም “ስህተቶችን” ሲፈጽም ተስተውሎዋል። አዎ! የሚዲያ ተቋማት በተለይም ካገር ውጭ ሆነው የሚሰሩ ከሆነ አልፎ አልፎ የተሳሳተ መረጃ ለህዝብ ሊያደርሱ ይችላሉ። ተቋማቱ የሚገመገሙት ግን ባሰራጯቸው የተሳሳተ ዜና ልክ ሳይሆን፣ ያስተላለፏቸው ዜናዎች በተሳሳተ ማስረጃ የተደገፉ ወይም ከተሳሳተ ምንጭ የተቀዱ መሆናቸውን ወዲያውኑ ለሕዝብ አሳውቀው ይቅርታ በመጠየቃቸው ነው። “በስህተት የሚተላለፈው” ዘገባ ግን በተደጋጋሚ የሚያነሳው አንድን ጉዳይ ወይም በአንድ ቡድን ላይ ያተኮረ ከሆነ፣ የሚዲያ ተቋሙ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው። በዚህ መልኩ ESAT የብቃት ወይም የአቋም መመዘኛውን መስፈርት አያሟላም ባይ ነኝ። እስዎ ዝም ብለው ያላንዳች ማስረጃ OMNን ከ RTLM ጋር እንዳያያዙት ሳይሆን ሁለት ተጨባች መረጃዎቼን ብቻ ላቅርብና ከ ESAT እና ከ OMN የትኛው የተሳሳተ መረጃ ሆን ብሎ ለአድማጮች በማቅረብ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት ጥረት እንደሚያደርግ እንይ። በነገራችን ላይ ይህንን “ክሴን” ሳቀርብ ዓላማዬ ከስዎ ለየት ያለ ነው። እኔ ESAT እስከ ዛሬ ባቀረባቸው “የጥላቻ ንግግሮች” ወይም “አንድን ብሄር በሌላው ላይ ለማነሳሳት” ሆን ብሎ ስለፈጸማቸው የወንጀል ተግባራት ምክንያት ይከሰስ ወይም ተቋሙ ይዘጋ የሚል ዕብደት አይከጅለኝም። የግል ሚዲያ ባልተለመደበት ኋላ ቀር አገራችን እንደ ESAT እና OMN ያሉ ሌሎችም ተጨማሪ የግል ሚዲያ ተቋማት ያስፈልጉናል። ዋናው ነገር፣ የተቋሙ ሠራተኞች፣ ከመጀመርያው በሙያቸው የተካኑ እንዲሆኑ፣ ወገንተኝነት እንዳያጠቃቸውና ሆን ብለው የተሳሳተ ወይም የተጣመመ መረጃን ለሕዝብ እንዳያቀርቡ፣ በድንገት የተሳሳተ መረጃ ካቀረቡ ደግሞ ወዲያውኑ ይቅርታ የሚጠይቁ እንዲሆኑ ማሳሰብ የኛ ኃላፊነት ይመስለኛል። ወደ ክሶቼ ልመለስና!
ESAT አውቆ በድፍረትም ሆነ ሳያውቅ በስሕተት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለከፍተኛ ግጭት ሊዳርግ የሚችል የጥላቻ መልዕክት አስተላፏል የምላቸውን ሁለት ማስረጃዎቼን ላቅርብ፣
ማስረጃ አንድ፣ በሃምሌ ወር 2008 ዓ/ም ከአማራ ክልል “በጽሁፍ” የደረሰውን “ትኩስ ዜና” ታውቂው የ ESAT ጋዜጤኛ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፈው ዜና፣ የአማራ ሕዝብ በወያኔ ላይ ስላወጀው ጦርነት ያወሳና፣ “የትግራይ ሕዝብ ወያኔ እንደማይወክለው ተረድቶ ከአማራ ወንድሞቹ ጎን ተሰልፎ የወያኔ ኤሊቶችን እንዲወጋ የቀረብለትን ጥሪ ችላ ማለቱ አልበቃ ብሎት፣ “ልጆቻችን ስለሆኑ ከጎናቸው አንለይም” በማለታቸው “ወደድንም ጠላንም ምርጫው አንድ ብቻ ነው፣ ….. የተበላሸን ዓሳ ከባሕር ማስወገጃ መንገዱ አንድ ነው፣ የባሕር ውሃን ማስወገድ ነው!” ብለው መወሰናቸውን ለህዝብ “አብስሯል”። በቀላል አማርኛ፣ ወያኔን ለመደምሰስ የአማራ ሕዝብ ያለው ብቸኛ አማራጭ የትግራይን ሕዝብ መደመሰስ ነው ማለት ነው። ባንድ ሕዝብ ላይ የጅምላ ግድያና ጭፍጨፋ ማወጅ ማለት ትርጉሙ ይኸው ነው። አዎ! የ ESAT አመራር፣ የተላለፈው መልዕክት በስህተት መሆኑን አምኖ ከድህረ ገጻቸው ላይ ከጥቂት ሰዓቶች በኋላ አንስተውታል። ግን ዘግይተዋል። በዛሬ የቴክኖሎጂ ዘመን፣ መረጃ አንዴ ካፍ ከወጣ መመለስ የማይቻልበት ጊዜ ስለሆነ ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ተለጥፎ፣ የትግራይ ሕዝብም በሰማው ቁጥር በ ESAT ላይ ያለውን የጥላቻ ትኩሳት እየጨመረ ሲሄድ፣ እኔም ለማስረጃነት ይኸው እየተጠቀምኩበት ነው። ደግነቱ ግን ከዓቅም ማነስ ይሁን ወይም በሆነ ተዓምር ምክንያት በትግራይ ሕዝብ ላይ የታወጀው የጅምላ ጭፍጨፋ አልተተገበረም። “በቀጥታ ካገር ቤት እንደደረስን ያስተላለፍነው ዜና ስለሆነ ይዘቱን ለመርመር ጊዜ አላገኘንም” የሚለው የ ESAT ማስተባበያ ግን ውኃ አይቋጥርም። ጋዜጤኛው “የተላከለትን ጽሁፍ” ስቱዲዮ ቁጭ ብሎ ከማንበቡ በፊት የድርጅቱ የተክኖሎጂ ባለሙያዎች ከደብዳቤው ይዘት ጋር የሚጣጣም ቪዲዮዎችን ከESAT መዝገብ ቤት ጎልጉለው በማውጣት ከንባቡ ጋር አዋህደው ስላቀረቡ፣ “የተሳሳተ መረጃው” ለሕዝብ የደረሰው ይዘቱን ለመመርመር ጊዜ አጥሮን ነው የሚለውን “ምክንያታቸውን” ውድቅ ያደርግባቸዋል።
ማስረጃ ሁለት፣ በሶማሊያ ክልልና በአጎራባቹ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ የብዙ ዜጎች ነፍሳት መጥፋቱ የሚታወስ ነው። ግጭቱን አስከትሎ ቁጥራቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሁለቱም ብሄር ተወላጆች ተፈናቅለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ESAT ኖቬምበር ወር 2018 ዓ/ም፣ የብዙ ሰዎች ሬሳ ባንድ ላይ ተከምሮ የሚያሳየውን ዘግናኝ ቪዲኦ ለሕዝብ አቅርቦ፣ ሬሳው የሶማሌዎች ሲሆን ገዳዮቹ ደግሞ ኦሮሞዎች ናቸው ብሎ ተረከ። የቴክኖሎጂ ጠበብት ኋላ እንዳረጋጡልን ከሆነ ግን፣ ቪዲዮው፣ በሰኔ ወር ላይ በካሜሩን በተፈጠረው የርስ በርስ ግጭት ጊዜ የተገደሉትን የካሜሩን ዜጎችን ሬሳ የሚያሳይና የቪዲዮውም ኦሪጂናል ቋንቋ በካሜሩን ከሚነገሩት ቋንቋዎች አንዱ እንደ ነበር ነው። የ ESAT ይህንን የተሳሳተ ዘገባ፣ ምንጩን ሳያጣራ ለሕዝብ ያቀረበበትን ዓላማ ምን እንደሆነና ለምንስ ይህን ያህል ጥረት ተደርጎበት የኦሪጂናሉ ቪዲዮ ቋንቋ ደምስሶ በኦሮሚኛ ተካው ስለሚለው መልስ ባይኖረኝም፣ ድርጊቱ ግን ሆን ተብሎ አንድን ሕዝብ በሌላው ላይ አነሳስቶ አስከፊ ለሆነ የርስ በርስ ዕልቂት ለመዳረግ ነው የሚል ግምት አለኝ። የ ESAT “ሌሎች ያሠራጩትን ይዘቱን በደንብ ሳንመረምር ያስተላለፍነው ዘገባ ነውና ይቅርታ ይደረግልን” ማለት፣ ሰውዬውን የገደልኩት አውሬ መስሎኝ ነውና ይቅርታ ይደረግልኝ የማለትያህል ነው። የሞተ ሰው አይመለስም። በቪዲኦ ምስል የተደገፈ ዘገባ ደግሞ አንዴ ከታየ ለዘላለም በሰው አእምሮ ተቀርጾ የሚቀር ስለሆነ መልሶ እንዳልነበር ማድረግ አይቻልም። ተራ የተዛባ ወሬ ሲሰማ በሕዝቦች ሰላምና ጸጥታ ላይ የሚያደርሰው አደጋ ስለሌለ ያው ወሬ ነው ተብሎ ይታለፋል። ESAT “ሳላጣራ በስሕተት አስተላለፍኩት” ያለው የውሸት ቪዲኦ ዘገባ ዓይነት ግን በኦሮሞና በሱማሌ ክልል ኗሪዎች መካከል ሲካሄድ በነበረው ግጭት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ነበር። የሚገርመው ደግሞ፣ ይህንን ዘገባ ተከትሎ፣ በሶማሌ ክልል ብቻ ሳይሆን በጂቡቲ በሚኖሩ ኦሮሞ ስደተኞች ላይ የደረሰውን እልቂት ቢቢሲ በጥልቅ ሲዘግበው፣ ESAT ግን “አልሰማሁም” አለ።
በዛሬው ያገራችን ሁኔታ ሁሉም ነገር በብሄር መነጽር ብቻ በሚታይበት ሰዓት ይኸኛው ወይም ያኛው ህዝብ በዚህኛው ወይም በዚያኛው ላይ ይህንን ወይም ያንን ወንጀል ፈጽሟል ብሎ የተሳሳተ መረጃን ማቅረብ፣ በቀላሉ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጭ መሆኑ ታውቆ ESATም አስፈላጊውን ዕርምት ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። በየርስ በርስ ግጭት አሸናፊ ስለማይኖር፣ ከዚህ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የማነሣት እኩይ ተግባር ተቆጥበን መላው ያገራችን ሕዝብ እኩል አሸናፊ የሚሆንበትን ጎዳና ብንቀይስ ለሁሉም ይጠቅማል ባይ ነኝ። ጊዜያችንን አጥፍተን ለጥፋት የሚረዳን ምስል እያቀረብን ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ወይም በሕዝቦች መካከል ጥላቻን ከመዝራት ይልቅ፣ ያንኑ ጭንቅላት ለበጎ ተግባር ብናውለው አገራችን ምንኛ በተጠቀመች! በሆነ ምክንያት ጭንቅላታችንን ለበጎ ነገር ማዋል ካቃተን ወይም ካልፈለግን ደግሞ ከዚህ ከባሕር ማዶ የሞቀ ቤታችን ቁጭ ብለን በቴክኖሎጂ ዕርዳታ የተሳሳተ ምስልን፣ የችግር ቅርጫትን ተሸክሞ ማራገፊያው ጠፍቶት እያቃሰተ ላለው ወገናችን አቅርበን ለርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳሳ ከመቀስቀስ ብንቆጠብና ዝም ብለን ባጋጣሚ ያገኘነውን ሰላማዊ ኑሮያችንን እዚሁ ባህር ማዶ ሆነን ማጣጣሙን ብንቀጥልበት የተሻለ ነው ባይ ነኝ

(TW)

Leave a Reply

Your e-mail address will not be published. Required fields are marked *