Fayyaan Mataa, Fayyaa Waa Maraa ti!

የግጭት አዘጋገብ መርሆዎች

በቀጄላ ቀና

ግጭት ለጋዜጠኞች እጅግ ፈታኝና ሙያዊ ማንነታቸው በተግባር የሚፈተንበት ወቅት ነው፡፡ የመረጃ እጥረት፣ ምንጭ በተፈለገ ጊዜ አለመገኘት፣ የምንጭ ታማኝነት ጥያቄ ውሰጥ መግባት፣ የተዛቡ ወይም ለማረጋገጥ የሚያስቸግሩ መረጃዎች መናፈስ ፣ የአሉበልታ መንሰራፋትና የኤዲቶሪያል ጣልቃገብነት ችግሮች የጋዜጠኞች የሙያና የሥነምገባር ብቃት ውስንነቶች ላይ ተጨምረው ችግሮቹን ያወሳስባሉ፡፡ በመጨረሻም ሙያው ከቆመለት አላማ ውጭ ሰለባ ወይም ራሱ የግጭት መሳሪያ ይሆናል፡፡ አሁን በአገራችን እየተሰተዋለ ያለውም ይህ ነው፡፡
በሚዲያ የሚዘገብ መረጃ በተቀባዮች ዘንድ በተለያዬ ሁኔታ ተተረጉሞ ስራ ላይ ይዉላል፡፡ ለምሳሌ የግጭት ተሳታፊዎች ካለባቸው ጊዜያዊ ስጋት የተነሳ የሚያገኙትን ማንኛውም መረጃ በተረዱት መጠንና ከራሳቸው ፍላጎት አንጻር ብቻ በመተርጎም ለፈለጉት ፍጆታ ያዉሉታል፡፡ በዚህ ሂደት ውሰጥ በጥንቃቄ ያልተጠናቀረ መረጃ ያልተጠበቀ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሩወንዳ እ.ኤ.አ በ1994 ለ100 ቀናት በዘለቀው ጀምላ የዘር ፍጅት አንድ ሚሊዮን ሩዋንዳዊያን ባለቁበት ወቀት ሚዲያ ትልቅ አስተዋፅኦ አንደነበረው እናስታውሳለን፡፡
እናም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሁሉም የአገራችን ጋዜጠኞች ብሄራዊ፣ ሃይማኖታዊ ፣ ፖለቲካዊ ወይም ማህበረሰባዊ ማንነታቸውን በመወገን ሳይሆን ሙያዊ ሥነምገባርና መርሆዎችን መሰረት አድረገው መስራት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ጋዜጤኛች በሚሰሩት ሥራ የተቐማቸውና የራሳቸው ሙያዊ ማንነት ይፈረጃል፡፡ በማይሰሩት ወይም መስራት በማይፈልጉት ወይም በሚተውት ክስተትም እንዲሁ፡፡ አድማጭ-ተመልካች ወይም አንባቢ ግን ሁሌም ወገን ሳይለይ ከሚዲያ ትክክለኛና ያልተዛባ ወቅታዊ መረጃ ይጠብቃል፡፡

የጋዜጠኝነት መርሆዎች አካል የሆኑ የተወሰኑ የግጭት ወቅት አዘጋገብ ሥነምግባሮችን:-
1. የስራችን ውጤት ማንንም ወገን መጉዳት የለበትም
 ድጋፍ ወይም ተቃውሞ የሚያስተጋቡ የውግና ዜናዎች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ግጭትን ልያባብሱ ስለሚችሉ ማስወገድ
 ያልተረጋገጠ መረጃን ከመጠቀም መታቀብ፡፡ ሰዎች ስለነገሩን ብቻ መረጃውን አምኖ መቀበል ለስህተት ያጋልጠናል፡፡ በግጭት ወቅት ሰዎች የመሰላቸውን ይናገራሉ፡፡ ጋዜጠኛ መረጃውን በትክክል ሳያረጋግጥ መዘገብ የለበትም፡፡ የግለሰቦች አስተያዬት በራሱ ብቻውን ዜና አይሆንም፡፡
 የባለስልጣናት ወይም የግለሰቦች አስተያየትና የቃላት አጠቃቀም በህበረተሰቡ ውስጥ መከፋፈልና ጥላቻን አንዳይፈጥሩ የአርትዖት ሥራን በጥንቃቄ መፈጸም አለበት፡፡ በግጭት ወቅት ማንኛውም መረጃ ከሚያሳድረው አሉታዊና አወንታዊ ተጽዕኖ አንጻር ተመዝኖ መታየት አለበት፡፡
 ከማንኛውም ወገን ቢሆን በሰው ልጅ ላይ አደጋ እንዲከተል የሚያደርግ መረጃ በፍጹም መሰራጨት የለበትም፡፡
 መረጃን መደበቅ ወይም መከልከል ወይም እንዳይዘገብ ማድረግ ግጭትን ባልተጠበቀ ሁኔታ ሊያባብስ ስለሚችል ጋዜጠኞች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለህብረተሰቡ የተረጋጋ ህይወት የሚጠቅሙና ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ የሚያበረታቱ ዘገባዎችን ቸል ማለት የለባቸውም፡፡
 የግጭት ሰለባዎችና ተሳታፊዎች ማንነት በሚገለጽበት ጊዜ ብሄራዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ ሙያዊ ወይም ቤተሰባዊ ማንነታቸውን በዝርዝር ማቅረብ አደገኛ ብቻ ሳይሆን ግጭቱን የማባባስና ወደ ከፋ ደረጃ የማድረስ ኃይል አለው፡፡ በኣንድ በኩል የግጭት ሰለባዎች ወገን በማንነታቸው ተነጥለው የተጠቁ የሚያስመስል ሲሆን በሌላ በኩል አጥፊዎች ማንነታቸውን ተመክተው ጥቃት እንደፈጸሙ አድረጎ ይስላል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውና ተከባበረው አብረው የሚኖሩ ሰዎች መሃል ያልተገባ ስጋትና መጠራጠር ይፈጥራል፡፡ በመጨረሻም ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አልፎ አልፎ እየታየ ያለው ግጭት ማንነትን መሰረት አደረጎ የተፈጠረ ነው ብሎ መደምደም ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ሰው በመሆናቸው የደረሰባቸውን ወይም ያደረሱትን ከመዘገብ ዉጭ ድርጊታቸውን ከማንነታቸው ጋር ማያያዝ ተገቢ አይሆንም፡፡ ግጭት ብዙ ጊዜ ወንጀል የታከለበት ደረጊት ያስከትላል፡፡ ማንም ማንን ወክሎ ወንጀል ስለማይፈጽም ጥንቃቄ የሻል፡፡ ግጭት ጊዜያዊ ችግር ስለሆነ ያልፋል፡፡ ህዝብ ግን ለዘላለም አብሮ ኖራል፡፡ ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ጠባሳ መፍጠር የለብንም፡፡
2. ከመረጃ እና አሉባልታ ሰጣገባ ራስን ማራቅና ማንኛውንም መረጃ በሙያዊ ሥነምግባር ብቻ መገምገም
 ለጋዜጠኝነት ሙያ ሥነምግባር ተገዢ ሆኖ መስራት፡፡ በግጭት ወቅት በምንም አይነት መልኩ ለማንም አመለካከት አለመወገን የስፈልጋል፡፡ አሁን በስፋት አየተሰተዋለ ያለው የውግና ዘገባ ሕዝቡን ግራ የሚያጋባና ወደማይፈለግ ስጋትና አሉባልታ የሚወስድ ነው፡፡ ከዚህ የሚጠቀም ማንም አይኖርም፡፡ የጋዜጠኛ ሥራ እውነትን መሻትና መዘገብ እንጂ መወገን አይደለም፡፡
 የአንድ ወገን ስጋት ወይም ጉዳት ላይ ብቻ ከማተኮር የሁሉም ወገን ጉዳት ፣ ስጋትና ሃዘን በአግባቡ በጥንቃቄ ማስተናገድ ያስፈልጋል፡፡ የግጭት ተሳታፊዎች ተጠቂም ሆኑ አጥቂ ሁሉም የአንድ አገር ዜጎች ናቸውና፡፡ በግጭቱ ምክንያት የደረሰዉን አጠቃለይ ጉዳት ለመግለጽ ግምት ከመጠቀም የሚመለከተውን ባለሙያ መጠየቅና መብራራት
 የሚፈርጁ ወይም የሚያስጠቁ ቃላትና ቅጽል ከመጠቀም መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ወይም ገድያ፣ ንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰ አሰቃቂ ወንጀል፣ ጭካኔ፣ አረመኔያዊ ድርጊት፣ ጠላት …ወዘተ ተጎጂውን ወገን ወደማይፈለግ ቁጭትና ብቀላ ሊያነሳሳ ስለሚችል ከእንደነዚህ ቃላት መታቀብና የተፈጸመውን እውነታ ብቻ ለይቶ መዘገብ ያስፈልጋል፡፡
 በግጭት አካባቢ የሚገኙ ሁሉም ወገኖች የአሉባለታ ሰለባ እንዳይሆኑ ትክክለኛ መረጃ በፍጥነትና በተደጋጋሚ እንዲያገኙ ማደረግ ያስፈልጋል፡፡ አሉባለታዎች የሚሰተጋቡት የመረጃ ክፍተት ሲኖር ነው፡፡
 ትክክለኛና ዝርዝር መረጃ ከአስተያየትና ኮመንተሪ ተለይቶ መቅረብ አለበት፡፡ ጋዜጠኞች የራሳቸውን ኮመንተሪ ወይም የሌሎችን አስተያየትና ትንታኔ በዘገባቸው ስያካትቱ በእዉኔታው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማስተዋል አለባቸው ፡፡ ግነት ፣ ትችት፣ ማውገዝ ፣ ድጋፍና ተቃውሞ የሚስከትል ከሆነ እወነታውን ስለሚያዛባ ቢቀር ይመረጣል፡፡

3 ከግጭት ወሬና አሉባልታ ራስን ማራቅ
 ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ጎሳ ተኮር የድርጊትና የባህሪ ደምዳሜዎች (stereotypes) በግጭት ውሰጥ የገቡትን ወገኖች ክብር የማሳነስ ኃይል አለው፡፡ በተጨማሪም በዚህ ሁኔታ በሚፈረጁ ዜጎች ላይ የጥላቻና የመጠራጠር አመለካከት እንዲሰፋፋ ያረጋል፡፡ በመጨረሻም ችግሮችን ያባብሳል፡፡ በመሆኑም በግጭት ጊዜ በበጎም ይሁን በክፉ የእገሌ ብሄር ወይም ጎሳ አባላት እንዲህ ሆኑ ወይም እንዲህ አደረጉ ብሎ መዘገብ ሙዊ አይደለም፡፡ ይህ መቆም አለበት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ በኢትዮጵያዊ ማንነታቸው መጥራትና መዘገብ ይቻላል፡፡
 ግጭትን የሚቀሰቅሱ ወይም የሚያባብሱ ማናቸውንም ፕሮፖጋንዳዎች በሚዲያ ኣለማስተናገድ፡፡
 ስሜት የሚነኩ ቀስቃሽ ቃላትና አባባሎችን እንዲሁም ምስሎች አለመጠቀም፡፡ ለምሳሌ አረመኔያዊ ድርጊት፣ ኃላቀር አባባል፣ የሰው ደም የጠማቸው፣ ፍጹም አውሬነት ፣ በጠራራ ፀሀይ ሰው መፍጅት… ወዘተ እውነታውን ከማጋነን ያለፈ ፋይዳ የለቸውም፡፡
 እርስበርስ የሚጋጩ መረጃዎች ወይም መግለጫዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ እስከ መጨረሻው በመሄድ ትክከለኛውን መረጃ ቆፍሮ ለህዝብ ማቅረብ የስፈልጋል፡፡ በግጭት ወቅት የሚጣረሱ መረጀዎችን እንደወረደ በማቀረብ ህዝቡን ግራ ማጋባት ተገቢ አይደለም፡፡
 ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖችን እንደመረጃ ምንጭ በምንጠቀምበት ጊዜ ደህንነታቸው ችግር ላይ እንዳይወድቅ ጥንቃቄ ማደረግ ያስፈልጋል፡፡
 በግጭት ወቅት ሆሰፒታሎች፣ ፖሊስ እና የፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እና የህብረተሰብ መሪዎች ዋነኛ የመረጃ ምንጮቻችን ስለሆኑ በየጊዜው ግንኙነት በማደረግ ራስን በወቅታዊ መረጃ ማበልጸግ ያስፈልጋል፡፡ የሚያጠራጥረን መረጃ ካጋጠመም ማጣራት ከእነርሱ ይጀምራል፡፡
4 የህዝቡን ባህል ፣ ሃይማኖት ፣ እምነትና ወግ ማክበር
 በግጭት ውሰጥ ሁሉም ወገን የራሱን ነገር አጉልቶ ማዬትና የሌላውን ከራሱ ጥቅምና ማንነት አንፃር የመገምገም ባህሪ ስላለው የሚዲያ ዘገባ የሁሉንም ወገን የማንነት እሴቶች ማክበር አለበት፡፡
 ለግጭት አሰተወጽኦ የሚያደርጉ፣ መቻቻልና ገንቢ ውይይቶች አንዳይኖሩ እንቅፋት የሚሆኑ ልማዶችና ሁኔታዎች በስፋት ተፈትሸው መዘገብ አለባቸው
 ባህል ፣ ወግ፣ ሃይማኖት፣ አምነት እና ሙያ የመሳስሉ እሴቶች በምንም መልኩ በራሳቸው የግጭት መነሻ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
5 ሁሉንም ወገን በእኩል ማስተናገድ
 ግጭት ከመከሰቱ በፊት የነበሩትን መልካምና ሰላማዊ የህዝብ ለህዘብ ግኑኝነቶች በሁሉም ወገን ዕይታ መተንተንና ጠቃሚ ገጽታውን ማቀረብ
 ግጭት ከተከሰተ በኃላ የተፈጠረው ችግር፣ የሻከረው ግንኙነት ፣ ያስከተለው ስጋት፣ ያለው ተስፋ፣ የህዝቡ የሰላም ፍላጎትና የመፍትሄ አቅጣጫ የመሳሰሉ ጉዳዮች ከሁሉም ወገን እይታና ፍላጎት አንጻር መስተናገድ አለበት
 በግጭት ያልተሳተፉና እንደገለልተኛ የሚወሰዱ ካሉ የእነርሱም ድምጽ መሰማት አለበት፡፡
 Provide diverse perspectives, which includes covering events from all possible angles, bringing in opposing views, giving voice to the discriminated and marginalized individuals and groups is an important instrument of overcoming conflict inciting moves
 በግጭት ዘገባ ጊዜ በሁሉም ወገን ዘንድ ተቀበይነት ለማግኝት መሞከር ያስፈልጋል፡፡ አንድ ወገን በዘገባችን ወዶን ሌላ ወገን የሚጠላን ከሆነ እኛም ሰለባ ሆነናል ማለት ነው፡፡
 የውግና ዘገባ ማስወገድ

Source: Qajeelaa Qannaa