Fayyaan Mataa, Fayyaa Waa Maraa ti!

የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈፀም የተጠረጠሩት ግለሰቦች እና ተቋማቸው ጉዳይ

በባለፈው ሳምንት በእነ ጎሃ አፅበሃ መዝገብ የተካተቱ 33 ተጠርጣሪዎች ላይ በነበረው አራት ተከታታይ ቀጠሮዎች (ከታህሳስ 16—19/2011) ተገኝቼ የታዘብኩትን እና የተሰማኝን ላካፍላችሁ ወደድኩ።
[በእነ ጎሃ አፅበሃ መዝገብ የተካተቱት 33 ተጠርጣሪዎች በብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት የደህንነት ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል የሽብር ወንጀሎች መርማሪዎች/ሃላፊዎች እና የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ሆነው ሲሰሩ የነበሩ የተካተቱበት ነው። እነዚህ ግለሰቦች ከህግ አግባብ ውጪ ሰዎችን በመያዝ፤ በኦነግ፣ አግ7፣ ኦብነግና በሃይማኖት አክራሪነት ትፈለጋላችሁ በማለት ግለሰቦችን አፍኖ ጨለማ ቤት ውስጥ በማሰር እና የተለያዩ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት በማድረስ እንዲሁም፤ ተጠርጣሪዎች በፍርድ ቤት ትእዛዝ ማረሚያ ቤት ውስጥ እንዲቆዪ ሲደረግ ግለሰቦችን ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ጨለማ ቤት ውስጥ በማሰር በመደብደብ እና በማሰቃየት የሁለት ሰው ህይወት እንዲያልፍ በማድረግ ዜጎቸ ከህግ ውጪ እንዲሰቃዩ አድርገዋል በማለት ፖሊስ አስሮ ምርመራ እያካሄደባቸው ይገኛል። ]
ችሎቱን ለመከታተል ጉዳዩን የሚከታተለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ችሎት በጊዜያዊነት የተሰየመበት ፍትህ አዳራሽ በር ስደርስ በርከት ያሉ የተጠርጣሪ ቤተሰቦችን ተመለከትኩ። ተጠርጣሪዎቹ አልደረሱም ነበር። ከተወሰነ ጥበቃ በኋላ ተጠርጣሪዎቹን የያዘ መኪና መጣ። አንድ በአንድ እየወጡ ወደ ችሎት ሲገቡ ቆሜ አየሁ። ግማሽ የሚሆኑት ኮፍያ፣ መነፅር ስከርፍ አድርገዋል። እንዳይለዩ መሆኑ ነው። ማእከላዊ በገባሁ ከአስር ቀን በኋላ አንድ ማታ ላይ አስጠርቶኝ ምርመራ አይሉት ውይይት፤ ውይይት አይሉት ተስፋ በማስቆረጥ አይነት ወሬ እስከ ለሊቱ ሰባት ሰአት ድረስ አውርተን አመራመሩ እንደተመቸኝ (ከሱ በፊት ሲመረምረኝ ከነበረው ግለሰብ ጋር አነፃፅሬው) ነግሬው ሁሌ እሱ እንዲመረምረኝ የተማፀንኩት እና በነጋታው ተቀይሮ ያለሁበት እስኪጠፋኝ ፀጉሬን ጨምድዶ በጥፊዎች ያናጋኝን ደህንነት አየሁት። ይህን ሰው ብዙዎችን በጥፊ በመማታት ይታወቃል። በቁመናው እና በመልኩ እንጂ በስሙ ሳይታወቅ እስኪታሰርበት ጊዜ ድረስ የቆየ ነው። ” ከጓደኞችሽ ጋር በመሆን ከሽብርተኛ ድርጅቶች ስልጠና እየወሰዳችሁ ኢህአዴግን በአመፅ ለመጣል ስትንቀሳቀሺ እንደነበረ እመኚ” እያለ ቁምስቅሌን ሲያሳየኝ የነበረን መርማሪ አየሁት። ፍርድ ቤት በታራሚዎች አያያዝ ላይ ለሚቀርብለት አቤቱታ እንዲያስረዳ ሲጠራ መጥቶ አይኑን በጨው አጥቦ የሚዋሸው እና የፍርድ ቤት ትእዛዝን የማያከብረው የቂሊንጦ ሃላፊ አየሁት። ሌሎቹንም የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች፣ መርማሪዎች እና ደህንነቶች ሲገቡ ንዴት የተሞላው መጥፎ ትዝታ (ትዝታ ብቻ ለማለት ይከብዳል) ውስጥ ሆኜ ቆሜ ተመለከትኳቸው። ከተበዳይ ወገን በጣት የምንቆጠር ብቻ ነበርን ችሎቱን ለመታደም የመጣነው። ሁላችንም ተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ነበርን። በሌላው አንፃር ቤተሰቦቻቸውን እጃቸውን እያውለበለቡ እየተጠራሩ በቅርብ ርቀት ሰላምታ ይለዋወጣሉ። በዚችው ቅፅበት ይህን የጊዜ ቀጠሮ የችሎት አውድ እኔና ጓደኞቼ በሽብር ተጠርጥረን ከነበረን የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አውድ (ሌሎች በሽብር ተጠርጥረው ጊዜ ቀጠሮ አራዳ ሲቀርቡ ለነበሩም ይሰራል) ጋር ልዩነቱን ማሰብ ጀመረ አይምሮዬ።
እኛ: የምንቀርበው አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት
እነሱ: ልደታ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት
እኛ: ከማእከላዊ ጀምሮ እጃችን በካቴና ታስሮ ዳኛ ፊት ስንቀርብ ነው የሚፈታው
እነሱ: ከሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ጀምሮ ፍርድ ቤት ድረስ እስኪመጡም አይታሰሩም። ባጭሩ መቼም በካቴና አይታሰሩም [ቤተሰቦቻቸው በካቴና ታስረው አያዩአቸውም። አለም አይደል እንዴ ጃል?! እኛን ታስረን ያዩ ቤተሰቦቻችን/ጓደኞቻችን ያነቡት እንባ ታወሰኝ ]
እኛ፡ ከቤተሰቦቻችን/ጓደኞቻችን ሰላም እንዳንባባል እኛ ከምናልፍባት መንገድ በግምት 10 ሜትር የሚሆን ርቀት ላይ እንዲቆሙ ይደረጉ ነበር። አንዳንዴም ለሰላምታ እጅ መዘርጋት ከቁጣ እና ስድብ አንስቶ እስከ በዱላ ያስመታ ነበር። በአይን መተያየታችን አንዳች መልእክት የሚያስተላልፍ እየመሰላቸው መተያየትም ይከለክላሉ። ስልክ በእጅ ስለያዙ ብቻ ፎቶ አንስታችኋል በሚል የታሰሩ ወዳጆች አሉን። እነሱን እንዳናይ/እንዳያዩን በጓሮ ወስደውን በአጥር በኩል አሾልከው ያወጡንም ጊዜያቶች ነበሩ። ቤተሰቦቻችን/ጓደኞቻችን ስንገባ ባዩን በኩል የምንወጣ መስሏቸው ሲጠብቁን ያመሻሉ። [በወቅቱ የነበራችሁ ትዝ ይላችኋል መቼም]
እነሱ: ቤተሰቦቻቸውን ሁለት ሜትር ከሚሆን ርቀት ማየት እና ሰላም ማለት ማዋራት ይችላሉ። ቤተሰቦቻቸውን ሰላም ብላችኋል፣ ፎቶ አንስታችኋል ብሎ የሚናገርባቸውም ሆነ በክፉ የሚያይባቸው የለም።
እኛ: ከማእከላዊ አጅበውን አራዳ የሚያመጡን ፌደራሎች ብዛት እጅግ በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ ለሚያያቸው ሰው በጣም ያስፈሩ ነበር።
እነሱ: የሚያጅቧቸው ፌደራሎች ብዛት የላቸውም።
እኛ: የችሎት ቀጠሯችንን እንዲታደም የሚፈቀድለት አካል የለም። አንድ ጊዜ ብቻ ከሁላችንም አንድ የቤተሰባችንን አባል ብቻ ችሎት እንዲገባ/እንድትገባ ተፈቅዶልን ነበር። አራዳ ፍርድ ቤት ለጊዜ ቀጠሮ ቀርቦ ቤተሰብ ወይም ጓደኛ ወይም ጋዜጠኛ ችሎቱ ለተመልካች ክፍት የነበረ በሽብር ወንጀል ተጠርጣሪ የሚኖር የለም።
እነሱ: ችሎታቸውን ቤተሰቦቻቸውን እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ማንም ሰው መታደም ይችላል። ሊያውም ጉዳዩን የሚያየው ችሎት ስለሚጠብ ተብሎ ዳኞች ፍትህ አዳራሽ እየተሰየሙላቸው።
ካመጣቸው መኪና ወጥተው ችሎት እስኪገቡ በነበረችው ደቂቃ ይህን ልዩነት አየሁ። ፍርድ ቤት ቀርበው ከማያውቁት ጋር እና በድብቅ እስር ቤት ታስረው ከነበሩት ጋር ያለውን ልዩነት ደግሞ ማስላት ቀላል ነው። በእኛ ወይም በሌሎች የደረሰው ለምን በነሱ አልደረሰም አልልም። ሊደርስባቸው ይገባል ብዬም አላምንም። በመታሰራቸው ብቻ በሰፈሩት ቁና እንደተሰፈሩ አድርጎ በመቁጠር የሚደሰት (እስቲ ሲያደርጉ የነበሩትን ይዩት የሚል) በሌላ ወገን ደግሞ የሚከፋ (ለምን ይቅር አይባሉም ወይም ሲያደርጉት የነበረ ነገር ሁሉ እንደተፈፀመባቸው የሚያስብ) መኖሩን ሳስብ ይገርመኛል። በሽብር ተጠርጥረን/ተከሰን የነበርን እስረኞችን እስር አስከፊ የሚያደርጉት ይደርስብን የነበሩ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳቶች በተጨማሪ፤ በቤተሰቦቻችን፣ ጓደኞቻችን እና ጠበቆቻችን እንዳንጎበኝ የሚፈፀምብን ደባ፣ ቤተሰባችንን/ጓደኞቻችንን የማንቋሸሽ፣ የመሳደብ፣ የማንከራተት፣ አለፍ ሲልም መማታት እና ሌሎች እኛን እና ቤተሰባችንን/ጓደኞቻችንን ተስፋ የማስቆረጥ/የማስፈራራት ተግባሮች ናቸው። እነዚህ ነገር በሌሉበት በሰፈሩት ቁና ተሰፍረዋል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ይዞ መደሰት ወይም መከፋት አግባብ አይደለም። እነዚህ ሰዎች በሰፈሩት ቁና ሊሰፈሩ አይችልም። በአሁን ወቅት በሰፈሩት ቁና እንዲሰፈሩ የሚያደርግ አሰራርም ያለም አይመስለኝም።

የችሎቱ ሂደቱ በወፍ በረር

ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበረው ቀሪ ምርመራዎችን ለማከናወን በሚል ነበር። በተሰጠው ቀጠሮ መርማሪ ፖሊስ የሚቀሩት ስራዎች እንዳሉ ገልፆ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ለችሎቱ አመልክቷል።
  • ተጨማሪ የተጎጂ እና የምስክሮችን ቃል መቀበል
  • ተጎጂዎች በብዛት የሚገኝባቸው በባለፈው ጊዜ ቀጠሮ ውስጥ ያልሄድንባቸው ከተሞች ላይ የምርመራ ቡድን ልኮ ተጨማሪ የተጎጂዎች ቃል መቀበል የሚሉት ፤ መርማሪ ፖሊስ በቀጣይ የምርመራ ጊዜ ሊያከናውን ካቀደው በከፊል ይገኙበታል። ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀበትን ደብዳቤ እዚህ ላይ ይገኛል።
መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድለት አይገባም፤ ስራውን በአግባቡ እየሰራ አይደለም የዋስትና መብታችን ተከብሮ በውጪ ሆነን ልንከራከር ይገባል ሲሉ 33ቱም ተከሳሾች ጠበቃ ያላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት የሌላቸው በራሳቸው ሃሳባቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ያነሷቸው ሃሳቦች

  • “ከታሰርን 48 ቀናችን ነው። ከመያዛችን በፊት ምርመራው እንደተጀመረ በሚዲያ ሲነገር ነበር። በ 10/11/2010 ነው የተጀመረው። አምስት ወር ሆኖታል ማለት ነው ምርመራው ከተጀመረ። እንዴት ይሄን ያክል ጊዜ ይፈጃል? እኔ 24 ዓመት በመርማሪነት ሰርቻለው። አንዲት ቀን እንኳን በዲሲፕሊን ወይም ሌላ ጥፋት ተጠይቄ አላውቅም። ” ም/ኢ/ር የሱፍ ሃሰን
  • “…… መርማሪ ፖሊስ እስካሁን መረጃ ሰብስቦ አለማጠናቀቁ ወንጀል አለመሰራቱን እና የኔን ንፅህና ያሳያል። የምሰራበት መስሪያ ቤት መመሪያ እና የዜጎች ቻርተር አለው። በዚያ ተጠይቄ አላውቅም።” ዋ/ሳ ርእሶም ክህሽን
  • ” ትላንት የተወቀስንበትን ማስረጃ ሳትሰበስቡ ታስሩናላችሁ ወይ? …ከደህንነት መስሪያ ቤት ጋር በጋራ ትሰራላችሁ ተብለናል። በጋራ መስራታችን እንደ ሃጢያት መቆጠር የለበትም። የፀረ ሽብር ህጉ የሚያዘው ነው። ህጉን እኛ አላወጣነውም። ሁላችንም ሃላፊነታችንን ባልተወጣንበት አግባብ ነው እኛ ብቻ ተለይተን እዚህ ያለነው። እኛ ደብድበን ነው ማስረጃ የምናገኘው ከተባለ አቃቤ ህግ ለምን ማስረጃውን ይቀበለናል? ክስ ከሶ ሲያከራክር የነበረው አቃቤ ህግ ነው። መጀመር ከነበረበትም ከራሱ ከአቃቤ ህግ ነው። በመንግስት እና ህጋዊ ተቋም ሆኜ የሰራሁት ስራ ነው። ተቋሙ መቆጣጠር የለበትም ወይ? ተቋሙን ጨምሮ እኔም መጠየቅ አለብኝ።…. ” ም/ኮ/ር አለማየሁ ሃይሉ
  • ” አርብ ተይዘን ሰኞ ነው መጀመሪያ ፍርድ ቤት የቀረብነው። …ደህንነት እና ፖሊስ አሁንስ አብረው እየሰሩ አይደለም ወይ? … እኔን እንድሰራ ያዘዘኝ ቢሮ አለ። ከተጠየቀ እንደ ስርዓት ነው መጠየቅ ያለበት።” ም/ኢ/ር ምንላርግልህ ጥላሁን
  • “የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚባል ወንጀል የለም። ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ብትቀበልም የምታስፈፅምበት ግን የተለየ ህግ የላትም። ነው ወይስ እኛን አስራችሁ ህግ ልታወጡ ነው?” ስሙን የረሳሁት ተጠርጣሪ
  • “ፖሊስ ቀጠሮ ለመጠየቅ ያቀረበው ምክንያት በጅምላ እና የእያንዳንዳችንን በሚያሳይ መልኩ አይደለም።” ሁሉም ተጠርጣሪዎች
  • “መርማሪዎች ቃላችንን አልተቀበሉንም።” አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች
ችሎቱ ከላይ ያሰፈርኳቸውን እና መሰል ሃሳቦች ከተጠርጣሪዎቹ በሁለት ቀን በተሰየመው ችሎት ከሰማ በኋላ የመርማሪ ፖሊስን ምላሽ ሰምቶ እና የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ከመረመረ በኋላ በ19/4/2011 ትእዛዝ አስተላልፏል። ለጊዜ ቀጠሮ ፖሊስ ከዘረዘረው ምክንያት በከፊል መቀበላቸውን ዳኞች ገልፀው የተሰሩት ስራዎች በእያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች ተለይቶ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ፖሊስ ታዟል። ከተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮም ከ1ኛ እስከ 16ኛ ላሉት ተጠርጣሪዎች የ10 ቀን ቀጠሮ (ለነገ ታህሳስ 26/2011) ብቻ ተፈቅዷል። ከ17ኛ እስከ 33ኛ ላሉት ተጠርጣሪዎች ደግሞ የተጠየቀው 14 ቀን (ለታህሳስ 30/2011)ተፈቅዷል። 19ኛ ተጠርጣሪን (ዋ/ሳ እቴነሽ አረፈአይኔ) በተመለከተ ከባለፈው ቀጠሮ በኋላ የተሰራ ስራ ስለሌለ እና ካለችበት ሁኔታ አንፃር (ህፃን ልጅ ይዛ በመታሰሯ) የጠየቀችው የዋስትና መብት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ 30ሺ ብር ስታሲዝ እና ከሃገር እንዳትወጣ የሚያግድ ደብዳቤ ስታመጣ እንድትፈታ ታዟል።

ለምርመራ ስራው የተሰጠው ትኩረት

ግለሰቦቹ (እነ ጎሃ አፅበሃ) የተጠረጠሩበት ወንጀል ካደረሰው ጉዳት አንፃር የምርመራው እና የፍርድ ቤቱ ሂደት ተገቢውን ትኩረት አግኝቷል ብዬ አላምንም። በመጀመሪያ ደረጃ ሌሎች ጉዳዮችን የማያይ የተለየ በባለሙያ እና አማካሪዎች የታገዘ የመርማሪ ቡድን ሊቋቋም ይገባ ነበረ። ይህም የመርማሪዎችን ስራ ከማቅለሉም ባሻገር፤ ማስረጃዎችን በበቂ ሁኔታ ለማጠናቀር ይረዳል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የሚሰጡት የ10 ቀን እና 14 ቀን ቀጠሮዎች መሰራት ላለበት ስራ በቂ ናቸው ማለት አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ በዚህኛው ቀጠሮ የመጀመሪያ ቀን በ16/4/2011 የ14 ቀን ቀጠሮ ፖሊስ ጠየቀባቸው። በተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ላይ ተከሳሾች አስተያየታቸውን ሲሰጡበት እና ክርክሮች ሲደረጉ ትእዛዝ እስኪሰጥ ድረስ አራት ቀን ፈጅቷል። መርማሪ ፖሊሶቹ በአራቱም ቀን ፍርድ ቤት ቀርበው ሲከራከሩ ነው ጊዜውን ያሳለፉት። ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሲፈቅድላቸው ግን ከመጀመሪያው ቀን ቀጠሮ የሚቆጠር በማለት ነው። ቢቻል ቢቻል የደርግ ባለስልጣናትን ጉዳይ ካየው የልዩ አቃቤ ህግ ፅ/ቤት ጋር የሚመሳሰል ተቋም መመስረት ነበረበት። በእርግጥ ክስ የመመስረት ሂደቱ ገና ስለሆነ ልዩ አቃቤ ህግ ለማቋቋም አሁንም ጊዜው የረፈደ አይመስለኝም።
የመንግስት ብሮድካስት ሚዲያዎች (የግል ሚዲያዎችም ሊሆኑ ይችላሉ) የፍርድ ሂደቱን በቀጥታ ማስተላለፍ አለባቸው ብዬ አምናለው። በቀጥታ ማስተላለፍ ባይቻል እንኳን ሰፋ ያለ ጊዜ ተሰጥቶት የፍርድ ሂደቱ ለህዝብ እንዲደርስ መደረግ ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚህ አንፃር ፋና ቲቪ ከሌሎች በተሻለ መልኩ የፍርድ ቤት ውሏቸውን ዘገባ በቋሚነት እያስተላለፈ ይገኛል። ቃና ቲቪም በአጭር የአየር ሰዐት ቢሆንም ዜናውን ተከታትሎ መዘገቡ ጥሩ ቢሆንም ሰፋ ያለ ጊዜ ተሠጥቶት ሙሉ ችሎቱን ለተመልካቾቻቸው ቢያደርሱ ተመራጭ ነው፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት የሽብር ችሎቶችን ሂደት በመከታተል የሚታወቁ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሃገራዊም ሆነ የውጪ ሃገር ድርጅቶች እና ኤምባሲዎች ችሎቱን መታዘብ ይኖርባቸዋል የሚል እምነት አለኝ።

ተቋማቶች የማይጠየቁት ለምንድነው?

ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል ተብለው ተጠርጥረው በእስር ያሉት በእነ ጎሃ አፅበሃ መዝገብ ያሉ 33 ግለሰቦችም የተጠረጠሩበትን ወንጀል የሰሩት ይሰሩበት በነበረው ህጋዊ የመንግስት ተቋም፤ ማለትም በብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት፣ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ሆነው ነው። መርማሪ ፖሊስ 33ቱ ግለሰቦች ወንጀሉን እንዴት እንደሰሩ ሲገልፅ “በድብቅ እና በስውር በመንግስት መስሪያ ቤት በመደራጀት እና በቡድን በመሆን …..” “ህዝብና መንግስት የሰጣቸውን ሃላፊነት በመተው ….. ” “የመንግስትን አወቃቀር በመጠቀም ….. ” “ከተሰጣቸው የህግ ተልእኮ ውጪ ….. ” የሚሉ ሃረጎችን ይጠቀማል። ያለተቋሙ እውቅና በህቡእ ተደራጅተዋል ለማለት ነው? ተቋሙ ሲሰራ የነበረውን ነገር አያውቅም ማለት ነው? አልገባኝም። ሆነም ቀረ ተቋሙ ሳያውቅ የተሰራ ወንጀል አይደለም። “24 ዓመታት በተቋሙ ስሰራ ተቀጥቼ አላውቅም”፣ “ያዘዘን ተቋሙ ነው” እና መሰል አስተያየቶች የሚያሳዩት ተቋሙ በተቋም ደረጃ የወንጀሉ ዋነኛ ተሳታፊ መሆኑን ነው እንጂ በህቡእ የተደራጁ ግለሰቦች መዋቅሩን ተጠቅመው የፈፀሙት አለመሆኑን ነው። በርግጥ ተቋም ሰው አይደለምና አይደለምና የተቋሙ ሃላፊዎች በተቋሙ ውስጥ ለተሰሩ ወንጀሎች ተቀዳሚ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። በዚህ መዝገብ ተጠርጣሪዎቹ ከተውጣጡበት ሶስት መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሁለቱ፤ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት እና የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮን (ማእከላዊን) ለረጅም ጊዜ በሃላፊነት የመሩ ግለሰቦች እስከዛሬ አልተያዙም። ተቋማቱም እስካሁን አልተጠየቁም። የተቋማቱን አፈፃፀም ይከታተል የነበረ የመንግስት ተቋምም አልተጠየቀም።
የኢህአዴግ ስልጣን ሲጠበቅ ግለሰቦች የሚጠቀሙት እንዳለ ሆኖ በዋነኝነት ተቋማቱ ይህን ወንጀል ሲፈፅሙ የነበረው ኢህአዴግን ከስልጣን እንዳይወርድ ለመጠበቅ ነው። ኢህአዴግ እንደ ድርጅት እና ሃገሪቱን ሲመራ እንደነበረ ፓርቲ በህግ መጠየቅ መቻል ነበረበት። ስልጣኑን ለማስጠበቅ ዜጎችን “አሸባሪ” እያለ እየፈረጀ መብታቸውን በተቋማት ደረጃ እንዲጣስ ሲያስደርግ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት ፤ አሁንም ስልጣኑን ለማስጠበቅ 180 ዲግሪ ተከርብቶ በተቋማት ውስጥ ይሰሩ የነበሩትን ግለሰቦችን “የዜጎችን ሰብአዊ መብት ጥሳችኃል” “በህጉ መሰረት ስትሰሩ አልነበረም” ” ህዝብ ስታሸብሩ ነበር” ብሎ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሲሰራ እሱም ከተጠያቂነት ማምለጥ የለበትም።
ኢህአዴግ እና ተቋማቶቹ በህግ ተጠያቂ መሆናቸው እንኳን ቢቀር የበደሏቸውን ሰዎች እና የኢትዮጵያን ህዝብ በግልፅ እና በአደባባይ ይቅርታ በመጠየቅ ነገሮችን ማጥራት አለባቸው። ጠ/ሚር አብይ ፓርቲያቸው/መንግስት ወንጀል ሲሰራ እንደነበረ እና ዜጎችን ሲያሸብር እንደነበረ የገለፁባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ይቅርታ ሲጠይቁ አልሰማሁም። እንዲያው በደፈናው “ህዝባችን ይቅር ብሎናል” ይበሉ እንጂ ህዝቡን ይቅርታ የጠየቀው አካል የለም። ተቋማቶቹም ሃላፊዎቻቸውን ቀየሩ እንጂ በተቋሙ ለተሰራው ወንጀል ይቅርታ ሳይጠይቁ ስራቸውን ቀጥለዋል።
የተጠርጣሪዎቹ ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው።
1. አቶ ጎሃ አጽበሃ ግደይ – የአዲስ አበባ የደህንነት ኃላፊ
2. አቶ አማኑኤል ኪሮስ መድህን – የሃገር ውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር
3. አቶ ደርበው ደመላሽ – የውስጥ ደህንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩና የኢኮኖሚ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ
4. አቶ ተስፋዬ ገብረጻዲቅ – የውስጥ ደህንነት ጥናትና የወንጀል ምርመራ መምሪያ ኃላፊ
5. አቶ ቢኒያም ማሙሸት – በውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ የኦፕሬሽን ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ (በዋናነት የግንቦት 7 ጉዳይ ክትትል)
6. አቶ ተሾመ ሀይሌ – የአማራ ክልል የደህንነት ኃላፊ የነበሩና የጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር
7. አቶ አዲሱ በዳሳ – በሃገር ውስጥ ደህንነት የኦሮሚያ ክልል ደህንነት ኃላፊ
8. አቶ ዮሃንስ ወይም ገብረእግዚአብሄር ውበት – የውጭ መረጃ
9. አቶ ነጋ ካሴ – በጸረ ሽብር መምሪያ የኦነግ ክትትል ኃላፊ
10. አቶ ተመስገን በርሄ – በጸረ ሽብር መምሪያ የኦነግና ኦብነግ ክፍል ዋና ኃላፊ
11. አቶ ሸዊት በላይ – በሃገር ውስጥ ደህንነት ኦፕሬሽን መምሪያ የግንቦት 7
ክትትል ምክትል መምሪያ ኃላፊ
12. አቶ አሸናፊ ተስፋሁን – በሃገር ውስጥ ደህንነት የአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደህንነት አስተባባሪ
13. አቶ ደርሶ አያና – በውጭ መረጃ የአማራ ክልል ክትትል
14. አቶ ሰይፉ በላይ – በውስጥ ደህንነት የደቡብ ክልል ክትትል ኦፊሰር
15. አቶ ኢዮብ ተወልደ – በውስጥ ደህንነት የደቡብ ክልል ደህንነት ኃላፊ
16. አቶ አህመድ ገዳ – በውስጥ ደህንነት የኦሮሚያ ክልል ክትትል ምክትል ኃላፊ
17. ምክትል ኮማንደር አለማየሁ ሀይሉ ባባታ – ቀድሞ የፌደራል ፖሊስ የሽብር ወንጀል ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር የነበረና ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ያገለገለ
18. ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሀሰን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
19. ዋና ሳጅን እቴነሽ አራፋይኔ – የሽብር ወንጀል መርማሪ
20. ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ – የሽብር ወንጀል መርማሪ
21. ምክትል ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
22. ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን – የሽብር ወንጀል መርማሪ
23. ኦፊሰር ገብረማሪያም ወልዳይ
24. ኦፊሰር አስገለ ወልደጊዮርጊስ
25. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ
26. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረሐዋርያት – የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደህንነት ኃላፊ
27. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተክላይ ኃይሉ – የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሰራተኛ
28. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አቡ ግርማ – የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ኃላፊ የነበረና በዝዋይ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ
29. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አዳነ ሐጎስ – የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሰራተኛ
30. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተስፋሚካኤል አስጋለ – በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከፍተኛ የደህንነት ባለሙያ
31. ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብራት መኮንን – የዝዋይ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደህንነት ኃላፊ የነበረና የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ጥበቃና ደህንነት ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ
32. ረዳት ኢንስፔክተር አለማየሁ ኃይሉ ወልዴ – በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መርማሪ
33. ረዳት ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ አየለ – በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መርማሪ